በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኪታሩት በኤርትራ ላይ የማጠቃለያ ሪፖርት አቀረቡ


ኤርትራ “ሃገራዊ አገልግሎት” እያለች የምትጠራውን የተራዘመ መርኃግብር እንድታቆም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ ጉዳይ ልዩ ዘጋቢ (ራፖርተር) ሼይላ ከታሩት አሳሰቡ፡፡

ልዩ ራፖርተሯ ለድርጅቱ ባስገቡት የመጨረሻ ወይም የማጠቃለያ በተባለ ሪፖርታቸው እርሳቸው ኃላፊነቱ ከተሰጣቸው ጊዜ አንስቶ የሰብዓዊ መብቶችን አያያዝ አስመልክቶ በኤርትራ አንዳችም መሻሻል አለመታየቱን አስታውቀዋል፡፡

ጄኔቫ የምትገኘው ሪፖርተራችን ሊሳ ሽላይን ባጠናቀረችው ዘገባ መሠረት የመንግሥታቱ ድርጅት መርማሪ ኤርትራ ውስጥ ተከታታይነት ያለው የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ መኖሩን፣ መሠረታዊ ነፃነቶች በብርቱ የተገሰሱ መሆናቸውን፣ ብዙ ጊዜም ሞትን ያካተቱ ወይም የሚያስከትሉ ቅጣቶች በዜጎች ላይ እንደሚፈፀሙ ዘርዝረዋል፡፡

ኪታሩት በዚሁ ለመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አስገቡት በተባለው ሪፖርታቸው ላይ “የዘፈቀደ እሥራቶች፣ እሥረኞች ከሰዎች ጋር እንዳይገናኙ አድርጎ መያዝ፣ አስገዳጅ ሥራ የታከለበት ብሄራዊ ወይም ሃገራዊ አገልግሎት ያለማቋረጥ እየተካሄዱ ያሉ ጥሰቶች ናቸው” ብለዋል፡፡ “ኤርትራ እነዚያን አድራጎቶችና የሃገራዊ አገልግሎት መርኃግብሯን በአስቸኳይ እንድታቆም ጥሪ አሰማለሁ - ያሉት ሼይላ ኪታሩት - ከታሰሩት በዘፈቀደ ተይዘው የሚገኙ፣ በተለይ ሕፃናትን፣ ሴቶችን፣ አዛውንትና የህሊና እሥረኞችን በአፋጣኝ እንድትፈታ እጠይቃለሁ” ብለዋል በሪፖርታቸው ላይ፡፡

በሌላ በኩል የልዩ ዘጋቢዋን ሪፖርት “አጥፊ፣ ተዓማኒነት የሌለውና ወገናዊ” ሲሉ በጄኔቭ የኤርትራ ጉዳይ ፈፃሚ የሆኑት አቶ በረከት ወልደዮሃንስ ብርቱ ወቀሳ ማሰማታቸውም ተዘግቧል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ “ፍትኀዊነት የሌለውና ፍሬ ቢስ” ብለው የጠሩት ሂደትም በአስቸኳይ እንዲቆም ሲሉ ለምክር ቤቱ ጥያቄ ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG