በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤርትራ - ለማዕቀቦቹ ምላሾች


አልሻባብን ጨምሮ ሌሎችም የሶማሊያ አማፂያንን ትረዳለች በምትባለው ኤርትራ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀቡን ማጥበቁ የተራዘመውን የሶማሊያን ብጥብጥ ሊያቀዘቅዘው ይችላል በሚል ተስፋ የጣሉ አሉ፡፡

የሚቀርቡባትን ውንጀላዎች የምትቃወመው ኤርትራ ግን ማዕቀቡን “ሕገወጥና ፍትሕ የጎደለው” ብላዋለች፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የትናንት፣ ሰኞ ውሣኔው በሶማሊያ ሠላምና መረጋጋት ፈጥኖ እንዲመጣ ያስችላል ብለው ከሚያስቡት መካከል አንዱ የሆኑት ወታደሮቻቸው እዚያው ሶማሊያ ውስጥ የሚገኙት የዩጋንዳው ጦር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ፌሊክስ ኩላዪግዬ “በመሠረቱ ማዕቀቦች የሚጣሉበትን ሃገር የገንዘብ ጡንቻ በማላላት አቅማቸውን ያዳክማሉ፡፡ በመሆኑም ኤርትራ ማዕቀቦቹ ካረፉባት በይዘታቸውም ሁሉን አቀፍ ከሆኑ ለአፍራሽ ተግባራት የምታውለው ትርፍ ሣንቲም አይኖራትም ማለት ነው” ብለዋል፡፡

የሶማሊያ ጎረቤቶች የሆኑት ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ዩጋንዳ ኤርትራ ለአልሻባብና ለሌሎችም ሶማሊያ ውስጥ ለሚንቀሣቀሱ፣ በዚያ የሚገኘውን የአፍሪካ ሕብረት ሠላም አስከባሪ ጦር (አሚሶም)ን ለሚወጉ ታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች ሲሉ ኤርትራን ለተራዘመ ጊዜ ሲወነጅሉ ይሰማሉ፡፡

ባለፈው ሐምሌ ኤርትራ ትሰጣለች ያለውን የፖለቲካ፣ የገንዘብ፣ የሥልጠናና የሎጂስቲክስ ድጋፍ የሚዘረዝር ሪፖርት አውጥቶ ነበር፡፡

ሣውዝሊንክ የሚባለው ፅ/ቤቱ ናይሮቢ የሚገኘው የምርምርና የጥናት ተቋም ኃላፊ የሆኑት አብዲዋሃብ ሼህ አብዲሳመድ በምዕራቡ የሚደገፉትና ከሶማሊያ አማፂያን ጋር እየተፋለሙ የሚገኙት ኃይሎች “በቅርቡ ትልቅ እፎይታ” ያገኛሉ ይላሉ፡፡

“ማዕቀቦቹ - አሉ አብዲሣመድ - ኤርትራ ለሶማሊያዊያኑ አማፂያን ድጋፍ የምታቀብልባቸውን ከአሥመራ ወደ ኪስማዩ የሚደረጉ በረራዎችን ይዘጋሉ፡፡”

በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ በኤርትራ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች በኤርትራ ሕዝብ ላይ ጎጂ ጫና እንደሚያሣድሩ በአፍሪካ ሕብረት የኤርትራ አምባሣደር ግርማ አስመሮም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ሀገሮች ለዕድገታቸው አንዱ በሌላው ላይ መተማመን ስለሚኖርባቸው ክልላዊ ቅንጅትን እንደምትደግፍ የተናገሩት አምባሣደር ግርማ “እኛ እነዚህን ሀገሮች አንዳቸውንም ለማናጋት አስበን አናውቅም። ምክንያቱም ለኛ የወደፊት ገበያዎቻችን፥ የሚጠቅሙን ናቸውና፡፡ እኛ የምንፈልገው ጠንካራ እና በዕድገት የምትራመድ ኢትዮጵያን ነው” ብለዋል፡፡

“ኤርትራ አልሸባብን እየደገፈች ናት” የሚለውን ክስ አምባሣደር ግርማ “ውሸት እና ማታለል” ሲሉ ውድቅ አድርገው ኤርትራ “አልሸባብን ደግፋ አታውቅም ወደፊትም አትደግፍም” ብለዋል፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG