በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤርትራ እና ኢጋድ ከ16 ዓመታት መለያየት በኋላ ጅቡቲ ላይ ተገናኙ


የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የጋራ ልማት ትብብር/ኢጋድ ጉባኤ ጅቡቲ
የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የጋራ ልማት ትብብር/ኢጋድ ጉባኤ ጅቡቲ

ለ16 ዓመታት፣ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የጋራ ልማት ትብብር/ኢጋድ/፣ ራሷን አግልላ የቆየችው ኤርትራ፣ በድጋሚ ኅብረቱን መቀላቀሏን፣ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል አስታወቁ።

አቶ የማነ፣ ትላንት ሰኞ፣ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፥ ሰባት አባል ሀገራት ያለው ቡድን ጅቡቲ ላይ ባደረገው የመሪዎች ጉባኤ፣ “ኤርትራ በኢጋድ ውስጥ የነበራትን እንቅስቃሴ መቀጠሏንና መቀመጫዋን መያዟን” ገልጸው፣ አገራቸው፥ ለሰላም፣ መረጋጋት እና ቀጣናዊ መዋሐድ ለመሥራት ዝግጁ እንደኾነች አመልክተዋል።

ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ በባጁት ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ አመራር፣ ዓምባገነን እንደኾነ የሚገለጸው የኤርትራ መንግሥት፣ እ.አ.አ. በ2007፣ ከኢጋድ አባልነት ራሱን ያገለለው፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት፣ ኅብረቱ ኬንያን እንድትከታተል መጠየቁን ጨምሮ፣ ተከታታይ አለመግባባቶች ከተፈጠሩ በኋላ ነው።

እ.አ.አ. በ1993፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተለየች በኋላ፣ ሁለቱ ጎረቤት አገሮች፣ ለሁለት ዓመታት የድንበር ጦርነት ያካሔዱ ሲኾን፣ እ.አ.አ. በ2018፣ የሰላም ስምምነት እስከሚደረግ ድረስ ግንኙነታቸው ሻክሮ ቆይቷል።

የኤርትራ፣ ቀጣናዊ ኅብረቱን የመቀላቀል ውሳኔ ይፋ የተደረገው፣ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ፣ በየካቲት ወር ኬንያን በጎበኙበት ወቅት፣ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ አገራቸው ቀጣናዊውን ተቋም የማነቃቃት ሐሳብ ይዛ ኢጋድን እንደምትቀላቀል ከአስታወቁ በኋላ ነው።

የ77 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ፣ በትላንት ሰኞው የጅቡቲ ጉባኤ ላይ ያልተገኙ ሲኾን፣ በምትካቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሣሌህንና አማካሪያቸውን የማነ ገብረ መስቀልን ልከዋል።

XS
SM
MD
LG