በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ዕሁድ ይሰበሰባል


የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አዲስ ሊቀመንበሩን ወደመምረጥ የሚወስደውን ስብሰባ ለማድረግ ለፊታችን ዕሁድ፤ መጋቢት 2/2010 ዓ.ም ቀጠሮ ያዘ።

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አዲስ ሊቀመንበሩን ወደመምረጥ የሚወስደውን ስብሰባ ለማድረግ ለፊታችን ዕሁድ፤ መጋቢት 2/2010 ዓ.ም ቀጠሮ ያዘ።

የኢሕአዴግ ፅሕፈት ቤት ኃላፊውን አቶ ሺፈራው ሽጉጤን የጠቀሰው አፍሪካ ኒውስ የሚባል የመላ አፍሪካ ዜና አውታር ባሠራጨው ዘገባ የገዥው ግንባር አራት አባል ድርጅቶች ያካሄዷቸውን የተናጠል ስብሰባዎችና ግምገማዎች ውጤቶች በዚሁ የዕሁዱ ስብሰባቸው ወቅት በጋራ እንደሚመክሩ አመልክቷል።

ከሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ስብሰባ በኋላ እንደሚካሄድ የተነገረው ከእያንዳንዱ አባል ድርጅት አርባ አምስት ተጠሪዎች የሚወከሉበት ባለ 180 አባል ምክር ቤት የሚመርጠው የግንባሩ ሊቀመንበር ለፓርላማው ቀርቦ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆንም ተገልጿል።

ለመጭ ለውጦች መንገድ ለመጥረግ በሚል ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን በቅርቡ ያሳወቁት የግንባሩ የወቅቱ ሊቀመንበርና የአባል ድርጅቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ደኢሕዴግ/ መሪ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እስኪታወቅና ሥልጣኑን እስኪረከብ ኃላፊነታቸውን እያከናወኑ እንደሚቆዩ ታውቋል።

አፍሪካ ኒውስ ባሠራጨው ዘገባ “እገሌ” ብሎ ስም አይጥራ እንጂ መጭው ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሮሞ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጭምጭምታ በሰፊው እንደሚናፈስ ጠቁሟል።

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦሕዴድ/ በቅርቡ የቀድሞ ሊቀመንበሩን ምክትል በነበሩት በዶ/ር አብይ አሕመድ መተካቱ ስትራተጂካዊ ውሣኔ ነው እየተባለም ሲሆን ኃይለማርያም ደሣለኝ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ከተረከቡ አንስቶ ምክትላቸው ሆነው እያገለገሉ ያሉት የሌላኛው የኢሕአዴግ አባል ድርጅት - ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ መሪ አቶ ደመቀ መኮንን መሆናቸው ይታወቃል።

የኢሕአዴግ መሪዎች አይቀበሉት እንጂ በግንባሩ ውስጥ ‘የበላይነት አለው’ የሚባለው ሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ /ሕወሓት/ም በቅርቡ ባካሄደው ሹም ሽር ጠንካራ እጆች እንዳሏቸው የሚነገረው አቶ ደብረፅዮን ገብረሚካኤልን ሊቀመንበሩ አድርጎ መምረጡ ይታወሳል።

ለገዥው ፓርቲና ለመንግሥቱም ቅርበት እንዳለው የሚታወቅ አንድ የሃገሪቱ መገናኛ ብዙኃን አውታርም የአቶ ሽፈራው ሽጉጤን መግለጫ አንተርሶ ባወጣው ዘገባ “ሃገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታና የጥልቅ ተሃድሶውንም አፈፅፀም መነሻ በማድረግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ያሳለፋቸው ውሣኔዎችና ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ያሉበትን ደረጃ ገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ጠቁመዋል” ብሏል።

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የምክር ቤቱ ስብሰባዎች እስከአሁን ሳይካሄዱ የቀሩት “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ በማድረግና፣ በሌላ በኩል ደግሞ የብሄራዊ ድርጅቶቹ የተናጠል ጉባዔዎችን ማካሄድ ወቅታዊ ክንዋኔዎች ስለነበሩ ነው” ሲሉ የኢሕአዴግ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ መግለፃቸውን የዜና አውታሩ አክሎ ዘግቧል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG