በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ ቅሬታ አቀረበች


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባውን ከግንቦት 21 እስከ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ/ም ካካሄደ በኋላ/ ፎቶ የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባውን ከግንቦት 21 እስከ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ/ም ካካሄደ በኋላ/ ፎቶ የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በአገራዊ ምክክሩ ላይ እንድትሳተፍ በይፋ የቀረበላት ጥያቄ አለመኖሩ እንዳሳዘነው ቅዱስ ሲኖዶስ ገለጸ፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያካሒድ የቆውን፣ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባውን ማጠናቀቁን አስመልክቶ፣ ዛሬ ኀሙስ ረፋድ ያወጣውን ባለ12 ነጥቦች መግለጫ፣ ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በንባብ አሰምተዋል፡፡

ሀገረ መንግሥትን ከመመሥረት ጀምሮ በአስታራቂነትና በሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ለኾነችው ቤተ ክርስቲያን፣ እስከ አሁን ድረስ ከምክክር ኮሚሽኑ በይፋ የቀረበ የተሳትፎ ጥሪ አለመኖሩን”

በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያቀረበው ቅሬታ፣ በመግለጫው ከተካተቱት ነጥቦች መካከል ሲኾን፣ “ሀገረ መንግሥትን ከመመሥረት ጀምሮ በአስታራቂነትና በሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ለኾነችው ቤተ ክርስቲያን፣ እስከ አሁን ድረስ ከምክክር ኮሚሽኑ በይፋ የቀረበ የተሳትፎ ጥሪ አለመኖሩን” ይገልጻል፡፡

ይህም ኾኖ፣ ኮሚሽኑ፥ የተሳታፊ ልየታንና አጀንዳ መረጣን አጠናቆ ወደ ምክክር ትግበራ እየገባ መኾኑ፣ ቅዱስ ሲኖዶስን ቅር ማሰኘቱን ፓትርያርኩ አመልክተዋል፡፡

በመኾኑም፣ ከአገራዊ ምክክሩ ጋራ በተያያዘ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አጀንዳ የማቅረብና የመሳተፍ መብት የሚያስከብር ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ መሠየሙን አቡነ ማትያስአስታውቀዋል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ ሊቃውንትና ምሁራን የተካተቱበትን ይህንኑ ኮሚቴ በኃላፊነት እንዲመሩም፣ የደቡብ ኦሞ እና አሪ ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መመደባቸውን የአሜሪካ ድምፅ ለማወቅ ችሏል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅሬታ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው፣ ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋራ ከመወያየታቸው አስቀድሞ የሚሰጡት ማብራሪያ እንደሌለ ገልፀው በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ የሰፈረውን ምላሽ እንድንመለከት ነግረውናል።

ኮሚሽኑ በጉዳዩ ላይ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ ኮሚሽኑ፥ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋራ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን አስታውሷል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱም በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስታደርግ መቆየቷን ገልጿል፡፡

ተሳትፎን በተመለከተ ጥሪ አልተደረገልንም፤”

በጉባኤው አማካይነት፣ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች ባሉ አህጉረ ስብከቷ፣ የሃይማኖት መሪዎችን በመመደብ፣ የተሳታፊ ልየታው ውጤታማ እንዲኾን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስታደርግ ቆይታለች፤ ብሏል ኮሚሽኑ፡፡

በቀጣይም፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋራ በቅዱስ ሲኖዱስ ጽሕፈት ቤት ድረስ በመገኘት ለመወያየት ዝግጁ መኾኑን ኮሚሽኑ አስታውቆ፣ ይኸው የአካታችነት መርሕ ከኹሉም የሃይማኖት ተቋማት ጋራ በእኩልነት እንደሚተገበርም ገልጿል።

በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ “ተሳትፎን በተመለከተ ጥሪ አልተደረገልንም፤” በሚል፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተጨማሪ፣ ከልዩ ልዩ የሃይማኖት ተቋማት እና የፖለቲካ ኀይሎችም ዘንድ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡

የአሜሪካ ድምፅ፣ በዚኹ ጉዳይ ላይ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት፣ የኮሚሽኑን ኃላፊዎች ለማናገር ሞክሯል፡፡ ኾኖም፣ ኮሚሽኑ ከአብያተ እምነት መሪዎች ጋራ ውይይት ከማድረጉ በፊት፣ በጉዳዩ ላይ ለብዙኀን መገናኛዎች ዝርዝር መረጃ እንደማይሰጥ ኃላፊዎቹ በመግለጻቸው አስተያየታቸውን ለማካተት ሳይችል ቀርቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG