ብሄራዊው የምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መሠረት ምርጫው ሙሉ በሙሉ በኢህአዴግ አሸናፊነት ቢጠናቀቅም፤ «ለታዛቢነት ያቀረብኳቸውና ደጋፊዎቼ ከሥራ መታገድ፥ ወከባና እንግልት እየደረሰባቸው ነው፤» ሲል፥ ተቃዋሚው የኦሮሞ ኅዝብ ኮንግሬስ ገዢውን ኢህአዴግን ወንጅሏል።
ችግሮቹ ተከሰቱ የተባለበት የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር በበኩሉ፥ «ለተቃዋሚው ወገን በምርጫ ታዛቢነት መንቀሳቀስም ሆነ ደጋፊ ወይም አባል መሆን የዜጎች መብት ነው፤ እናም በዚህ ሳቢያ በማንም ላይ ዕርምጃ አልተወሰደም፤» ሲል ውንጀላዎቹን አስተባብሏል።
«ማንም ሰው በምንም ዓይነት ሁኔታ እንዳይዋከብ፤ የልማት ሥራው እንዳይስተጓጎል ግልፅ የመንግስት መመሪያ ወጥቷል፤» ሲሉ፥ መንግስታቸውን የተከላከሉት የኦሮሚያ አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ የመረጃና ኅዝብ ግንኙነት ሥራ ሂደት መሪውን አቶ መስፍን አሰፋን ናቸው።
«ደጋፊዎቻችን ለስራ አጥነት እየተዳረጉ ነው፤» የሚሉት የኦሮሞ ኅዝብ ኮንግሬስ ዋና ፅህፈት ቤት ረዳት ኃላፊ አቶ ኦልባና ሌሊሳ ግን፤ ባለሥልጣናቱ ሳያውቁ የሚፈፀም ምንም እንደሌለ ተናግረው፤ ለችግር የተጋለጡት ወገኖች ከአንዱ የመንግስት ቢሮ ወደ ሌላው ለአቤቱታቸው ሠሚ ሳያገኙ እየተንከራተቱ ነው ብለዋል።
የተቃዋሚ ዕጩዎች፥ ስለ ተሸነፉበት ምርጫ ነፃና ትክለኛነት እንዲመሰክሩ፤ በተቃዋሚ የምርጫ ታዛቢነት የተሳተፉት ደግሞ ይቅርታ ጠይቀው ከፈረሙ ብቻ ስራቸውን የሚያገኙ መሆናቸው እየተገለፀላቸው መሆኑን አቶ ኦልባና ዘርዝረዋል።
«ለምሳሌ ያህል አቶ ጣሂር ደርሲሶ የተባሉ ታዛቢያችን በምርጫው ዋዜማና በዕለቱ ዕለት በወረዳው የኦህዲድ ፅ/ቤት የታዘዙ ሠዎች በአባታቸው ቤት ውስጥ በሰንሰለት አስረው በታዛቢነታቸው እንዳይሰሩ አድርገዋቸዋል፤» ሲሉ ከምርጫው አስቀድሞም ለተመረጡበት የታዛቢነት ሚና እንዳይበቁ በደጋፊቸው ላይ «ደረሰ፤» ያሉትን ህገ ወጥ ዕርምጃ የኦሮሞ ኅዝብ ኮንግሬሱ ተጠሪ በዋቢነት አንስተዋል።
ከምርጫው በፊትም ሆነ በምርጫው ወቅት እንዲህ ያሉት ተመሳሳይ ክሶች በተቃዋሚዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል፤ ነገር ግን ወደ ማጣራቱ ሲኬድ ዕውነተኛ ሆኖ አይገኝም፤ የሚሉት የኦሮሚያ አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ የመረጃና ኅዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መስፍን ደግሞ «የክሶቹን መሠረተ ቢስነትም ህዝቡ ያውቃል፤» ይላሉ።
በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች «እየተፈፀሙ ናቸው፤» የተባሉትን አንዳንድ ክሶች የሚያጣሩ መሆናቸውን አቶ መስፍን ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል አመልክተዋል።