በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የግንቦቱ ምርጫ ውጤት ይፋ ሆነ


ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ 544 መቀመጫዎች እንዳሸነፉ ቦርዱ አፅድቋል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መርጋ በቃና፣ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር፣ የፅሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ተስፋዬ መንገሻና የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ መሐመድ አብዱራህማን በተገኙበት መግለጫ የምርጫ ውጤቱን ትላንት ይፋ አድርጓል።

ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ዘርዝረውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ከተካሄደባቸው 547 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ኢህአዴግ 499 መቀመጫዎች፣ አብዴፓ 8 መቀመጫዎች፣ ሶህዴፓ 24 መቀመጫዎች፣ ጉኢህዴፓ 9 መቀመጫዎች፣ ገህዴን 3 መቀመጫዎች፣ ሀብል 1 መቀመጫ፣ አህዴድ 1 መቀመጫ፣ መድረክ 1 መቀመጫ፣ በግል 1 መቀመጫ ማሸንፋቸውን ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት ከ547 የፌዴራል ፓርላማ መቀመጫዎች ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ 544 መቀመጫዎች እንዳሸነፉ ቦርዱ አፅድቋል። ከክልል ምክር ቤቶች 1904 መቀመጫዎች ደግሞ ከ4 በስተቀር 1900 መቀመጫዎችን ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ እንዳሸነፉም ቦርዱ ይፋ አድርጓል።

ምርጫው ፍትሀዊና ነፃ እንዳልነበር ዋነኞቹ የሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገልፀዋል። መድረክና መኢአድ ምርጫው እንዲደገምም ጠይቀዋል። ኢዴፓ በበኩሉ ችግሮቹ ድጋሜ ምርጫ ከማካሄድ በላይ የሰፉ ናቸው፣ በመሆኑም ምርጫ የማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አስቸኳይ ድርድር መካሄድ አለበት ብሏል።

በተለይም ኢህአዴግ ከ99.6% በላይ ማሸነፉ ተቃዋሚዎቹን አላሳመነም። የቦርዱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ግን ውጤቱ እንደማያሳስባቸው ነው የሚናገሩት።

ማሸነፉ የፀደቀው ገዢው ፓርቲና የምርጫ ቦርዱ ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ እንደነበር ሲገልፁ ቆይተዋል።

XS
SM
MD
LG