በሜክሲኮ የኢሚግሬሽን ማቆያ ማዕከል፣ ሰኞ ዕለት በደረሰ የእሳት አደጋ፣ ቢያንስ 40 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ፣ ኤል ሳልቫዶር የማዕከሉን ሠራተኞች አድራጎት አጥብቃ አወገዘች፡፡
የፍልሰተኞች ማቆያ ማዕከሉ ሠራተኞች፣ አንድ ክፍል ውስጥ የነበሩትን ወንዶች፣ እሳቱ በተነሣበት ወቅት፣ ክፍሉ በጢስ ከመታፈኑ በፊት ለማስወጣት ሳይሞክሩ፣ ራሳቸው ከቃጠሎው ለማምለጥ ሲሯሯጡ እንደነበር፣ የማዕከሉ የደኅንነት ክትትል ቪዲዮዎች አሳይተዋል፡፡
የኤል ሳልቫዶር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ዛሬ ረቡዕ በአወጣው መግለጫ፣ ጉዳዩ ጥልቅ ምርመራ ተደርጎበት፣ ተጠያቂዎች ሕግ ፊት ይቀርቡ ዘንድ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል፡፡
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስ፣ “በዚኽ አሳዛኝ አደጋ ሕይወታቸውን ላጡት ሰዎች እንጸልይ፤” ሲሉ ተማፅነዋል፡፡
የእሳት አደጋው የደረሰው፣ ኩዊዳድ ሁዋሬዝ ውስጥ የሚገኝ ብሔራዊ የፍልሰተኛ ተቋም የሚያስተዳድረው ማዕከል ውስጥ ነው፡፡ ስፍራው፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች በብዛት ድንበር አቋርጠው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመግባት የሚሞክሩበት እንደኾነ ተነግሯል፡፡
በአደጋው የሞቱት እና የቆሰሉት ፍልሰተኞች፥ የጓቲማላ፣ የሆንዱራስ፣ የኤል ሳልቫዶር፣ የቬንዙዌላ፣ የኮሎምቢያ እና የኤኳዶር ሰዎች ሲኾኑ፣ የሚበዙት ጓቲማላውያን እንደኾኑ፣ የሜክሲኮ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ተናግሯል፡፡
የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት አንድሬስ ማኑዌል ሎፔዝ ላብራዶር በበኩላቸው፣ “ፍልሰተኞቹ፥ ከሜክሲኮ ልናስወጣቸው እንደኾነ ሲሰሙ ቃጠሎ አሥነስተዋል፤” ብለዋል፡፡
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ እንዲሁም፣ በሜክሲኮ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኬን ሳላዛር በደረሰው አደጋ ለሞቱት የፍልሰተኛ ቤተ ሰዎች፣ ኀዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ የሜክሲኮ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ምርመራ መክፈታቸው ተዘግቧል፡፡