በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢሰመጉ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈፀሙን አስታወቀ


ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታ ጋራ በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸሙን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ አስታወቀ።

ኢሰመጉ በክልሉ ተፈጽመዋል ካላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መካከል “በሻሸመኔ ከተማ ከመንግሥት የጸጥታ አካላት በተተኮሱ ጥይቶች የሰዎች ህይወት ማለፉን” በመረጃዎች አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ አጠቃላይ ስለደረሰው የጉዳት መጠን አልገለጸም፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገመቹ ለአሜሪካ ድምጽ በሰጡት አስተያየት፣ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ስለጉዳት መጠኑ እንደሚገልጹ ተናግረዋል፡፡

በተያያዘ በቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ መሰረት በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ትላንት የተጀመረው ጥቁር ልብስ የመልበስ ተግባር ዛሬም አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በሌሎችም ከተሞች የቀጠለ ሲሆን፣ ኢሰመጉ በዛሬው መግለጫው፣ “ከልብሱ ጋራ በተያያዘ በአንዳንድ አካባቢዎች ምዕመናን እስራት፤ እንግልት እና ወከባ እየደረሰባቸው ነው” ብሏል፡፡

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ መንግሥታቸው በቤተክርስቲያኗ ጉዳይ ገለልተኛ መሆኑን ቢገልጹም፣ ቤተክርስቲያኗ በበኩሏ መንግት “በሕገወጥነት የፈረጅኩትን አካል” እየደገፈ ነው ስትል ትከሳለች፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በዛሬው መግለጫው፣ “የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ያልሰጣቸው አዲስ የተሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት ወደ አብያተክርስቲያናት ሲገቡ በመንግሥት የጸጥታ አካላት ጭምር ታጅበው ነበር” ብሏል፡፡

ኃይማኖት የማኅበራዊ መስተጋብር አንዱ ክፍልና መብት በመሆኑ በመረዳት፣ “መንግሥት በቤተክርስቲያን እውቅና ያልተሰጣቸውን ኤጲስ ቆጶሳት በተለያዩ አብያተክርስቲያናት መመደብ አግባብ አይደለም” በማለት የተቃወሙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ላይ የጸጥታ አካላት የሚፈጽሙትን ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ ግድያ፣ አካል ማቁሰል፣ ድብደባ እና እስር፤ አንዲሁም ጥቁር ልብስ የለበሱ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ እስሮች አና ድብደባዎችን እንዲያስቆም፣ ከህግ አግባብ ውጪ የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የፈጸሙ የጸጥታ አካላትን ተጠያቂ እንዲያደርግ” ሲልም ኢሰመጉ ጠይቋል፡፡

የኢሰመጉን መግለጫ በተመለከተ ከመንግሥት በኩል እስካሁን በይፋ የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

በቤተክርስቲያኗ የተፈጠረው ችግር እየተባባሰ በሄደበት በዚህ ወቅት፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በደቡብ ወሎ ጉብኝት ላይ እያሉ በሰጡት አስተያየት “ችግሩ ከእልህ እና ከስሜት ውጭ በሆነ መልኩ በአማኞች መሪነት መፈታት አለበት” ሲሉ መናገራቸውን ከአማራ ሚዲየ ኮርፖሬሽን ዘግቧል፡፡

ከቤተክርስቲያኗ ወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮች ጎልተው የታዩበት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲስ፣ ከክልሉ መገናኛ ብዙኃን ኦቢኤን ጋር ባደረጉት ረዘም ያለ ቃለ መጠይቅ ስለጉዳዩ በቀጥታ አላነሱም፡፡ ይሁንና ርዕሰ መስተዳድሩ ትላንት በተሰራጨው በዚሁ ቃለመጠይቅ ላይ “ኢትዮጵያ ችግሮቿን ተሸግራ ወደ ሚፈለገው የብልጽግናና የአንድነት ደረጃ ላይ ትደርሳለች” ብለዋል፡፡

ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

ኢሰመጉ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈፀሙን አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:27 0:00

XS
SM
MD
LG