ከ2014 ዓ.ም. መስከረም እስከያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ፣ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዘጠኝ ዞኖች፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በኢ-መደበኛ የአማራ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ግጭት፣ በርካታ ያልታጠቁ ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፤ ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው ሪፖርቱ፣ ሲቪሎቹ ከሕግ አግባብ ውጭ የተገደሉት፥ “ለታጣቂዎች አልያም ለመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ድጋፍ ታደርጋላችሁ፤ ቤተሰቦቻችሁ የዚያ ወይም የዚያ ኃይል አባል ናቸው፤” በሚሉ ሰበቦች እንደኾነም ጠቅሷል።
በኦሮሚያ ክልል በተጠቀሱት ሁለት ዓመታት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ የጦር ወንጀልንና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን ሊያቋቁሙ እንደሚችሉ የጠቆመው ኮሚሽኑ፣ የተሟላ የወንጀል ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ብሏል።
በኢሰመኮ ሪፖርት የተጠቀሱት የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና ኢ-መደበኛ የአማራ ታጣቂዎች፣ ከዚህ ቀደም የቀረቡባቸውን መሰል ውንጀላዎች አስተባብለዋል።
የኮሚሽኑ የጅማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በዳሳ ለሜሳ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ በሰላማውያን ዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ሪፖርቱ ከወጣ በኋላም ቀጥለዋል።
በአገሪቱ የቀጠሉ ግጭቶችን ለመፍታት፣ ውይይት ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ እንደኾነም፣ ኮሚሽኑ ምክር ሐሳብ አቅርቧል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም