ከግብፅ ዋና ከተማ ከካይሮ ወጣ ብላ በምትገኘው ጊዛ ሰው በሚበዛበት ኢምባባ የተባለ አካባቢ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ላይ በደረሰ ቃጠሎ ቢያንስ አርባ አንድ ሰው መሞቱን የሃገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
እሳቱ የተነሳው በቤተ ክርስቲያኑ የአየር ሙቀት ማስተካከያ ውስጥ በተፈጠረ የኤሌክትሪክ ብልሽት ምክንያት መሆኑን እዚያው እንደነበሩ የተናገሩ ሰዎች ገልፀዋል።
አደጋው በደረሰበት ወቅት አቡ ሲፊን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አምስት ሺህ የሚሆኑ ምዕመናን እንደነበሩ ተገልጿል።
ከቃጠሎው ለማምለጥ በተፈጠረው ግፊያ መሃል የተረጋገጡ ሰዎች እንደነበሩና ከሞቱትም የሚበዙት ህፃናት መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቡሊና የጊዛ አስተዳዳሪ ጄነራል አህመድ ራሽድ ወደ ሥፍራው ሄደው በአደጋው ለተጎዱትና ለሟቾቹ ቤተሰቦች ኀዘናቸውን ገልፀው ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ቃል ገብተዋል።