የግብጽ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ባድር አብደላቲ ፍልስጤማውያን በቀየአቸው መቆየታቸውን የሚያረጋግጥ ፤ የግብጽ የጋዛ መልሶ ግንባታ እቅድ መዘጋጀቱን እና ነገ ማክሰኞ በካይሮ በሚካሄደው የአረብ ሀገራት አስቸኳይ ጉባኤ ለውይይት እንደሚቀርብ ትላንት እሑድ ተናገሩ።
ዩናይትድ ስቴትስ አካባቢውን እንደትቆጣጠር እና ፍልስጤማውያን ወደ ሌላ ቦታ ሄደው እንዲሰፍሩ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ያላቸውን ዕቅድ ፈጥነው የተቃወሙት የአረብ ሀገራቱ፤ሐሳቡን በዲፕሎማሲ ለመመከት በመሯሯጥ ላይ ናቸው ።
በእስራኤል እና በአሜሪካ በአሸባሪ ቡድንነት በተሰየመው ሐማስ መካከል በተደረገው ደካማ የተኩስ አቁም ስምምነት በጎርጎርሳውያኑ የካቲት አራት ቀን የታወጀው የትረምፕ ዕቅድ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ለረጅም ጊዜ መካከለኛው ምሥራቅን በሚመለከት ይዛው ከኖረችው ፖሊሲ ወደ ኋላ ያፈገፈገ ነው። ፖሊሲው ጎን ለጎን ሁለት መንግሥታት በመመሥረት ግጭቱን መፍታት ላይ ያተኮረ ሲሆን የአሁኑ የትረምፕ ዕቅድ በፍልስጥኤም እና በአረብ ሀገራት ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።
የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አብደላቲ፤ ግብጽ ላዘጋጀችው ዕቅድ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እና የገንዘብ ርዳታ እንደምትፈልግ በመጥቀስ በተለይም የገንዘብ ድጋፍን በተመለከተ አውሮፓ በሚኖራት ወሳኝ ሚና ላይ አፅንዖት ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ኅብረት የሜዲትራኒያን ኮሚሽነር ዱብራቭካ ሱይካ ጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ዕቅዱ በመጪው የአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ ከፀደቀ በኋላ ከዋና ለጋሽ ሀገራት ጋራ ጠንካራ ውይይት እናደርጋለን” ብለዋል።
መድረክ / ፎረም