የአረብ መሪዎች፤ ግብጽ በ53 ቢሊየን ዶላር ወጪ ጋዛን መልሶ ለመገንባት ያቀረበችውን ዕቅድ ትላንት ማክሰኞ አፅድቀዋል። እቅዱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለግዛቲቱ ካቀረቡት እቅድ በተለየ ፍልስጤማውያን ከአካባቢያቸው እንዳይፈናቀሉ ለማድረግ የሚያስችል ነው።
የግብፅ እቅድ ካይሮ ውስጥ በተካሄደው የመሪዎቹ ጉባዔ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ ተቀባይነት ማግኘቱን ፕሬዝደንት አብደል-ፈታህ አል ሲሲ ገልጸዋል።
በግብፅ አስተናጋጅነት በተደረገው ስብሰባ ላይ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የካታር አሚር እና የሳዑዲ አረብያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተገኝተዋል።
ትረምፕ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ውጪ አስፍሮ ሰርጡን መልሶ ለመገንባት ባለፈው ጥር ወር ላቀረቡት እቅድ አማራጭ ሆኖ የቀረበው የግብፅ እቅድ፣ ፍርስራሹ እስኪወገድ እና የተቀበሩ ፈንጂዎች እስከሚወጡ፣ የጋዛ ነዋሪዎች እዚያው ጋዛ ውስጥ በሰባት የተለያዩ ሥፍራዎች በጊዜያዊ መኖሪያ ቤቶች እንዲቆዩ ይጠይቃል።
በጉባኤው ላይ የግብጹ ፕሬዝደንት ሲሲ ትረምፕ ጋዛን መልሶ ለመገንባት ስላደረጉት ጥረት አመስግነው ግብፅ ያቀረበችው እቅድ ግዛቱን በጊዜያዊነት የሚመራ የአስተዳደር አካልንም ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪነት የፈረጀችው ሐማስ እቅዱን የተቀበለው ሲሆን፣ እስራኤል ግን ነቀፌታ ሰንዝራለች። የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ የአረብ ሀገራት ጉባኤ ያፀደቀው እቅድ ሐማስ እ.አ.አ በጥቅምት 7፣ 2023 ካደረሰው ጥቃት የተከተለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም ብሏል።
መድረክ / ፎረም