በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ግብፅ የኅዳሴ ግድብን ሦስተኛ ሙሌት ተቃወመች


ፎቶ ፋይል፦ ኅዳሴ ግድብ
ፎቶ ፋይል፦ ኅዳሴ ግድብ

ኢትዮጵያ ከዓባይ ተፋሰስ የግርጌ ሃገሮች ጋር ስምምነት ላይ ስትደርስ ኅዳሴ ግድብን ለሦስተኛ ጊዜ መሙላት ልትጀምር ነው ስትል ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ተቃውሞ ማቅረቧን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ።

በአፍሪካ አቻ የሌለው ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ይሆናል የተባለው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ በተለይ በኢትዮጵያና በሁለቱ የግርጌ ሃገሮች መካከል የውጥረትና የንትርክ ሰበብ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በዚህ ክረምት ግድቡን መሙላት እንደምትቀጥል የሚያሳውቅ ድብዳቤ ባለፈው ሣምንት ማክሰኞ ለግብፅ መላኳንና ካይሮም መልዕክቱ እንደደረሳት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መናገሩን ግብፅም የተቃውሞ አቤቱታዋን ይዛ ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት መሄዷን ኤኤፍፒ አክሎ ጠቁሟል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማከልም “ግብፅ ብሄራዊ ደኅንነቷን ለማስከበርና ወደፊት ኢትዮጵያ በተናጠል በምትወስዳቸው እርምጃዎች ምክንያት የሚመጡ አደጋዎችን ለመከላከል ህጋዊ መብቷን ተጠቅማ አስፈላጊውን እርምጃ ትወስዳለች” ብሏል።

የዛሬ አሥራ አንድ ዓመት የተጀመረው ከአራት ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀው የኅዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ 5000 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።

ዛሬ፤ ሰኞ ከግብፅ ባለሥልጣናት ጋር የተነጋገሩትና ባለፈው ዓርብ ኢትዮጵያ የነበሩት የዩናይትድ ስቴትስ አዲሱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሃመር የአሁን ጉብኝት ዝርዝር ለጊዜው ባይገለፅም ውይይቶቻቸው አጨቃጫቂውን የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ሳይጨምር እንደማይቀር ተነግሯል።

XS
SM
MD
LG