በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ግብፅ በቢሊዮን ዶላሮች አዲሱን ዋና ከተማዋን እያስፋፋች ነው


ፎቶ ፋይል፦ ካይሮ፣ ግብፅ
ፎቶ ፋይል፦ ካይሮ፣ ግብፅ

ግብፅ ከካይሮ በስተምስራቅ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በረሃ ላይ የምትገነባውን አዲስ ዋና ከተማዋን በእጥፍ ለማሳደግ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለማውጣት በዝግጅት ላይ መሆንዋን አስታወቀች፡፡

ይህን ያስታወቁት ፕሮጀክቱን በበላይነት የሚቆጣጠረው ኩባንያው ኃላፊ ካሌድ አባስ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ከስምንት ዓመታት በፊት ሥራ የጀመረው አዲሱ የአስተዳደር መቀመጫ የካይሮውን መጨናነቅ ለማቃለል እና እያደገ ያለውን 105 ሚሊዮን የግብፅ ሕዝብ በሚገባ እንዲያስተናግዱ በፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ ኤልሲሲ ከታለሙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው ተብሏል፡፡

የሚኒስትሮችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ከተጀመረ 8 ዓመታትን ባስቆጠረው ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ ወደ ተገነቡ አዳዲሶቹ ህንጻዎች እየተዛወሩ መሆኑን ተነግሯል፡፡

"በየቀኑ የሚመጡ ወደ 48,000 የሚጠጉ ሠራተኞች አሉን" ሲሉ የአስተዳደር መዲናው ከተማ ልማት (ACUD) ሊቀመንበር ካሌድ አባስ ባለፈው ማክሰኞ እኤአ ታህሳስ 26 ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን የሥራው ፍጥነት የቀዘቀዘ ቢመስልም የከተማዋ ምዕራፍ አንድ ባለ 70 ፎቅ ግንብ - በአፍሪካ ረጅሙ እና አምስት አዳራሾች ያሉት ኦፔራ ሃውስ፣ እጅግ ትልቅ የሆነ መስጊድ እና የመካከለኛው ምስራቅ ትልቁ ካቴድራል ያክትታል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ከምስራቅ ካይሮ የሚነሳ የኤሌክትሪክ ባቡር ባላፈው የፀደይ ወቅት ሥራ የጀመረ ሲሆን እስከ 100,000 የሚደርሱ መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ 1,200 ቤተሰቦች መግባታቸውንም ጨምረው ገልፀዋል። የግንባታው ምዕራፍ አንድ እና ሁለት ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ነዋሪዎችን እንደሚያስተናግድ ተነግሮለታል፡፡

በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 10 ኪሌሜትር የተዘረጋ ፓርክ ይኖረዋል የተባለው ይህ ፕሮጅከት ከአባይ ውሃ የሚቀዳ በየቀኑ 800ሺ ኪዪቢክ ሜትር ውሃ ይጠጣል ተብሏል፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ ሌላ 700, 000 ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚፈልግ አረንጓዴ ስፍራ እንደሚኖረውም ተነግሯል፡፡ ሁለቱ በድምሩ ከአባይ ወንዝ ድርሻ 1 ከመቶ (1%) ያህል የሚሆነውን ውሃ ያነሳሉ ተብሏል፡፡

የግብጽ ጦር ከፕሮጀክቱ 51 ከመቶ ድርሻ የያዘ ሲሆን የቤቶች ሚኒስትር 49 ከመቶ ድርሻውን በመያዝ በመጀመሪያው ምዕራፍ ብቻ ወደ 500 ቢሊዮን የግብፅ ፓውንድ በዛሬው የምንዛሪ ወደ 16 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መውጣቱ ተዘግቧል፡፡

ተችዎች በዚህ መንገድ ወደ ሠራዊቱ የሚዛወረው ሀብት እና ግብጽን ትልቅ ዕዳ ውስጥ ይከታታል ያሉት ፕሮጀክት ሥጋት ያሳዳረባቸው መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG