በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፍልስጥኤማውያን ከጋዛ ወደ ግብጽ እንዲወጡ እስራኤል ማስገደዷን ኤል-ሲሲ ተቃወሙ


ፎቶ ፋይል፦ የግብጽ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታ ኤል-ሲሲ፣
ፎቶ ፋይል፦ የግብጽ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታ ኤል-ሲሲ፣

የግብጽ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታ ኤል-ሲሲ፣ ፍልስጥኤማውያን፣ በሲናይ ልሳነ ምድር በኩል ከጋዛ እንዲወጡ፣ እስራኤል ለማስገደድ የምታደርገውን ጥረት ውድቅ እንዳደረጉት ገለጹ፡፡ ይህ ዓይነቱ ጥረት፣ ውሎ አድሮ ግብጽ ከእስራኤል ጋራ ያላትን ሰላም አደጋ ላይ እንደሚጥለው፣ ኤል-ሲሲ አስጠንቅቀዋል፡፡

በካይሮ፣ ከጀመርኑ መሪ ኦላፍ ሾልዝ ጋራ፣ ዛሬ ረቡዕ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ እስራኤል በጋዛ ላይ በጀመረችው ሙሉ ከበባ፣ የውኃ፣ የምግብ እና የነዳጅ አቅርቦትን መዝጋቷን ጨምሮ፣ ሰብአዊ ርዳታ ወደ ግዛቲቱ እንዳይገባ መከልከሏ፣ ፍልስጥኤማውያንን ወደ ግብጽ ለማባረር እንደታቀደ ስልት አድርገው እንደሚመለከቱት፣ ኤል-ሲሲ አስታውቀዋል፡፡

“ሲናይ፥ በእስራኤል ላይ ለሚሰነዘረው የአሸባሪዎች ጥቃት መስፈንጠሪያ ትኾናለች፤” ሲሉ ያስጠነቀቁት ኤል-ሲሲ፣ “እንዲህ ያሉት ጥቃቶች ደግሞ ግብጽን ተጠያቂ ያደርጋሉ፤” የችግሩን ተያያዥነት አሳስበዋል።

ኤል-ሲሲ፣ ግብጻውያን እኒኽን መሰል አካሔዶች እንደማይቀበሉት ገልጸው፣ እስራኤል የፍልስጥኤም ታጣቂ ቡድኖችን ለማጥፋት “ያወጀችውን ተልዕኮዋን” እስክትጨርስ ድረስ፣ ፍልስጥኤማውያንን ወደ ኔጌቭ እንድትወስድ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ የጀርመኑ መሪ ኦላፍ ሾልዝ፣ ሐማስ በእስራኤል ላይ የሰነዘረውን አሠቃቂ ጥቃት ተከትሎ፣ አገራቸው ከጎኗ መቆሟን እንደምትቀጥል መናገራቸውን አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG