በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እርዳታ ወደ ጋዛ መግባት ጀመረ


የግብፅ ቀይ ጨረቃ ተሽከርካሪዎች ጋዛ ሰርጥ ከዘለቁ በኋላ የፍልስጥዔም ቀይ ጨረቃ ሰራተኞች የእርዳታ እህሉን ከተሽከርካሪው እያወረዱ፤ እአአ ጥቅምት 21/2023
የግብፅ ቀይ ጨረቃ ተሽከርካሪዎች ጋዛ ሰርጥ ከዘለቁ በኋላ የፍልስጥዔም ቀይ ጨረቃ ሰራተኞች የእርዳታ እህሉን ከተሽከርካሪው እያወረዱ፤ እአአ ጥቅምት 21/2023

ውኃ፣ ምግብና መድኃኒት የጫኑ የግብፅ ቀይ ጨረቃ ተሽከርካሪዎች ዛሬ ወደ ጋዛ ሰርጥ መግባት ጀምረዋል።

እርዳታውን የጫኑት የመጀመሪዎቹ ሃያ መኪኖች ከበባ ውስጥ ወዳለው ሰርጥ የዘለቁት በግብፁ ራፋ ኬላ በኩል ነው።

የግብፅ ቀይ ጨረቃና የተባበሩት መንግሥታት ያበረከቱት እርዳታ ጋዛ ከገባ በኋላ የፍልስጥዔም ቀይ ጨረቃ እንደሚረከበው የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርቲን ግሪፊዝ ገልፀዋል።

በቅፍለቱ መካከል ስድሣ ቶን (ስድስት መቶ ኵንታል) ምግብ የጫኑ 3 ተሽከርካዎችን መላኩን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቆ 930 ቶን ተጨማሪ እርዳታ ለማስገባት የጭነት መኪኖቹ ራፋ ላይ እየጠበቁ መሆኑን አመልክቷል።

በሌላ በኩል ድንገተኛ አደጋና ነዋሪ ህመሞችን ለማከም የሚያስችሉ መድኃኒቶች የጫኑ አራት መኪኖች መግባታቸውን የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቆ ተጨማሪ አቅርቦቶች ግብፅ መከማቸታቸውንና ወደ ጋዛ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጿል።

ካይሮ ላይ እየተካሄደ ባለ የሰላም ጉባዔ ላይ ዛሬ የተናገሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ግብፅን ሁኔታውን ስለማመቻቸቷ አመስግነው እርዳታው በተፋጠነ፣ በሰፋ፣ ባልተቋረጠና ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ጋዛ ውስጥ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑንና እርዳታው በሰፋ ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ሲንዲ መኬን በፅሁፍ ባወጡት መግለጫ አሳስበዋል።

እርዳታው እንዲገባ የተወሰነ ስምምነት ላይ መደረሱን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተናገሩት ከትናንት በስተያ ረቡዕ ቴል አቪቭ ቢሆንም ቅድመ ሁኔታዎችን ግልፅ የማድረግና የተጣሉ ግዴታዎችን ውሱን የማድረግ ሥራዎች በግብፅ፣ በእሥራዔልና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል እስኪጠናቀቁ ተፈፃሚነቱ መዘግየቱ ተነግሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በራፋ በኩል ያለው የወሰን መተላለፊያ የመከፈቱን አጋጣሚ ለመጠቀም ከጋዛ ለመውጣት የሚሞክር ማንም የውጭ ሃገር ዜጋ በሁለቱም የድንበሩ አካባቢዎች ትርምስና ቀውስ የተቀላቀለበት ሁኔታ ሊያጋጥመው እንደሚችል በእሥራኤል የአሜሪካ ኤምባሲ አስጠንቅቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG