የትምህርት ጥራት ፈተና በተጋረጠባት ኢትዮጵያ፣ አንዳች ለውጥ ለማምጣት በማሰብ በግሉ ዘርፍ የተገነባ አዳሪ ትምህርት ቤት ነው፤ ኃይሌ ማናስ አካዳሚ፡፡ በወ/ሮ ርብቃ ኃይሌ እና በባለቤታቸው ጆን ማናስ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ የተገነባው ኃይሌ ማናስ አካደሚ፣ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ስፍራዎች በውጤት አወዳድሮ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተቀበላቸውን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡
መላውን ኢትዮጵያ ታሳቢ በማድረግ የተመሰረተው ትምህርት ቤቱ፣ አሁን ላይ 8ኛ ክፍልን ካጠናቀቁ በኋላ በሁለት ዙር የተቀበላቸው ሰባ ሁለት የ9ኛ እና 10ኛ ክፍል ተማሪዎች አሉት፡፡
“የነገዋን ኢትዮጵያ መሪዎች በጥራት ማፍራት” የትምህርት ቤቱ ዓላማ እንደሆነ ወ/ሮ ርብቃ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡
በዚህ አዳሪ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች፣ በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ የቀሰሙትን እውቀት በተግባር መፈተሸ የግድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለተግባር ትምህርት በተዘጋጁ እና አስፈላጊ ግብዓቶች በተሟሉላቸው ስፍራዎች የተግባር ልምምዶችን ያደርጋሉ፡፡ ትምህርታቸው በአብዛኛው ተግባር ተኮር መሆኑ የፈጠራ አቅማቸውን እንደሚያሳድግ ተማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎቹ በፅንሰ ሀሳብ እና በተግባር ያገኙትን ዕውቀት እና የሀሳባቸውን ውጤት፣ የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት የሚያሳዩባቸው ዝግጅቶችም ይካሔዳል፡፡ የተለያዩ ኪነጥበባዊ ተሰጥኦዎቻቸውንም በነዚህ ዝግጅቶች ላይ ያቀርባሉ፡፡
ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን የሚቀበልበት መስፈርት ብቃት ብቻ እንደመሆኑ፣ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል መመዘኛውን የሚያልፉ ተማሪዎች ትምህርት ቤቱን የመቀላቀል ዕድል አላቸው፡፡ ይህ ደግሞ የተለያዩ ማንነቶችን እና ባህሎችን በማወቅ፣ በታጊ ዕድሜያቸው ይበልጥ ኢትዮጵያዊ ሕብረ ብሔራዊነትን ለማወቅና ለመለማመድ እንደሚረዳቸው ተማሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡
የደርግ መንግሥት ወደ ሥልጣን በመጣ ማግስት ከአባታቸው ጋር ሀገራቸውን ጥለው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መሰደዳቸውን የሚገልጹት የትምህርት ቤቱ መስራች እና ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ርብቃ ኃይሌ፣ ለትውልድ ሀገራቸው አንዳች ነገር ማበርከት በማሰብ ትምህርት ቤቱን እንደከፈቱት ይገልጻሉ፡፡
በኃይሌ ማናስ አካደሚ መማር የሚፈልግ አንድ ተማሪ በዓመት 10 ሺ ዶላር/ከ500 ሺህ ብር በላይ መክፈል ቢጠበቅበትም፣ የትምህርት ቤቱን የመግቢያ ፈተና ወስዶ ያለፈ ተማሪ መክፈል ባይችል እንኳን እድሉ አይነፈገውም፡፡ ትምህርት ቤቱ ወጪውን በመሸፈን እንዲማር ያደርገዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በትምህርት ላይ የሚገኙትም ቢሆኑ፣ ገሚሱ በሙሉ ድድፍ የተቀሩት ደግሞ ቤተሰቦቻቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን አስተዋጽኦ እያደረጉ የሚማሩ ናቸው፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ብቁ የሆኑ “የነገዋን ኢትዮጵያ መሪዎች” ማፍራት ትርፋቸው መሆኑን የሚገልጹት የትምህርት ቤቱ መስራች፣ አሁን ባሏቸው ተማሪዎች ከወዲሁ ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን በማየት ላይ በመሆናቸው “ደስተኛ ነኝ” ይላሉ፡፡
ተማሪዎቹ ከመኝታ እና የምግብ አገልግሎት በተጨማሪ እንደ ጂምናዚየም እና ሕክምና ያሉ አገልግሎቶችንም በዚያው በትምህርት ቤታቸው ቅጥር ጊቢ ውስጥ የሚያገኙ ሲሆን፣ አብረዋቸው ከሚኖሩ መምህራን ጋር እንዲሁም እርስ በእርሳቸው ቤተሰባዊ ቅርርብ አላቸው፡፡