በኤኳዶር ታጣቂዎች ትናንት ማክሰኞ በቀጥታ ስርጭት ላይ በነበረ አንድ ቴሌቭዥን ጣቢያ በመግባትና ተኩስ በመክፈት በጋዜጠኞቹ ላይ ዛቻ ሲሰነዝሩ እና ሲያንገላቱ ተስተውለዋል።
‘ቲሲ ቴሌቪዥን ኔትወርክ’ በተባለው ጣቢያ ላይ የደረሰው ጥቃት ለ 15 ደቂቃ ያህል በቀጥታ ስርጭት ሲታይ ነበር።
በክስተቱ የሰው ሕይወት ባይጠፋም ቢያንስ አንድ ሰው ላይ ግን ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።
የቴሌቭዥን ጣቢያውን ያገቱትን 13 የሚሆኑ ታጣቂዎች ፖሊስ በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው ታውቋል።
ጥቃቱ የመጣው፣ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ዳንኤል ኖቦአ፣ አንድ የወሮበሎች መሪ አንድ እስር ቤትን ሰብሮ በመግባት ሰባት የፖሊስ አባላትን አግቶ መውሰዱን ተከትሎ የ60 ቀናት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ባወጡ ማግስት ነው። አዶልፎ ማሲያስ የተባለ የወሮበሎች መሪም ከእስር አምልጧል።
በአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎች መሪነት ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የነበረ ፋብሪሲዮ ኮሎን የተባለ ግለሰብም እንዲሁ ማምለጡ ታውቋል።
ፕሬዝደንቱ በአዋጃቸው 20 የሚሆኑ የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪ ቡድኖችን በሽብርተኛ ድርጅትነት ፈርጀዋል።
በሁከት የምትታመሰው ኤኳዶር፣ በደቡብ እና በሰሜን አሜሪካ መካከል ዋና የኮኬይን መተላለፊያ መሥመር እንደሆነች ይነገራል።
መድረክ / ፎረም