በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች “ራሳችንን ከታጣቂዎች ለመጠበቅ የገዛነውን መሳሪያ እንድናስረክብ ተጠየቅን፣ ይህ ደግሞ ለጥቃት ያጋልጠናል” ሲሉ ተናገሩ።
በዞኑ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩና ለአሜሪካ ድምጽ አስተያየት የሰጡ የአማራ ብሄር ተወላጆች፣ "ሸኔ" ብለው የጠሩት የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ታጣቂዎች ያደርሱብናል ካሉት ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል እንዲችሉ በመንግሥት ዕውቅና መሳሪያ ገዝተውና ታጥቀው መቆየያቸውን ተናግረዋል።
ሆኖም፣ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ ከትላንት በስቲያ እሁድ መጀመሩንና ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም. የመጨረሻ ቀን መሆኑን ጠቅሰዋል ።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ ለቪኦኤ በሰጡት ምላሽ፣ በሚልሺያ ወይም "ጋቸና ሲርና" በተባለው አደረጃጀት ያልተካተተ ማንኛውም ግለሰብ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይችል ተናግረዋል።
ትጥቅ ያላቸውን ነዋሪዎች ወደ መደበኛ የፀጥታ መዋቅሮች የማስገባት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል። “መንግስት ይሄንን ያደረገበት ምክንያት፣ ሕጋዊ አሠራርን ለመከተል እንጂ መሳሪያ ለመቀማት አስቦ አይደለም” በማለትም አክለዋል።
በዘገባው ላይ ስማቸው የተጠቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትና የፋኖ ታጣቂዎች አመራሮች ከዚህ ቀደም ለተመሳሳይ ውንጀላዎች በሰጧቸው ምላሾች ታጣቂዎቻቸው ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ እንደማያደርጉ በመግለፅ ማስተባበላቸው ይታወሳል።
መድረክ / ፎረም