የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ የኢንዶኔዥያ አገልግሎት ዘጋቢ ክሪቲካ ቫራጋር በቅርቡ ወደ ዋና ከተማዪቱ ጃካርታ ለመስክ ሥራ ተጉዛ በነበረ ጊዜ በዚያ ድንገት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን አገኘች። አነጋገረቻቸው፤ ታሪካቸውንም ፃፈች። የዘገባዋንም ርዕስ “የምሥራቅ አፍሪካ ስደተኞች ጃካርታን ላልተወሰነ ጊዜ ቤታቸው አደረጉ” ስትል ሰየመች።
ኦሮሞዪቱ ኢትዮጵያዊት ራና ሃያ አራት ዓመቷ ነው - ስትል ጀመረች የቪኦኤዋ ዘጋቢ ክሪቲካ የጃካርታ ዘገባዋን። ራና ስደተኞ ነች - የስደተኛ ሦስተኛ ትውልድ ቤተሰብ። ስትሰደድ ደግሞ ኢንዶኔዥያ ሁለተኛ ሃገር መሆኗ ነው፤ እግሮቿ የኢትዮጵያን ምድር በዚህ ለጋ ዕድሜዋ ለቅቀው ከተሰናበቱ።
የፖለቲካ ተቃዋሚና በስደት ላይ ከነበሩ አባቷ የተወለደችው ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ነው። ሳዑዲ አረቢያ የፖለቲካ ጥገኝነት ባለመስጠቷ ምክንያት ራና ሃገር የለሽ ሆነች። ይሁን እንጂ በ16 ዓመት ዕድሜዋ ከሳዑዲ አረቢያ በኃይል ተባርራ እንድትወጣ ተደረገና ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ ተገደደች። እዚያም የመጀመሪያ ዲግሪዋን እስክትይዝ ተማረች። የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ኦሮምያ ውስጥ ተቃውሞ ሲቀሰቀስ የመንግሥቱ ኃይሎች ይወስዷቸው በነበረ የብተናና የኃይል እርምጃዎች ምክንያት ደግሞ እንደገና ለስደት ተዳረገች - ጂቡቲ...
ራና ጂቡቲ ላይ ያሳለፈችው ጊዜ አጭር ቢሆንም ችግርና መከራ የበዛበት ነበር። ጥገኝነትና ከለላ ጠያቂ የሆኑ ኦሮሞዎች በመንግሥቱ ኃይሎች እየተከበቡና እየተያዙ ከሃገር ይባረሩ፣ ወደ ኢትዮጵያም እንዲመለሱ ይደረጉ ነበር - ራና ታሪኳን ለክሪቲካ ቫራጉር ማጫወቷን ቀጠለች።
በመሃል ታዲያ አንድ ሰዉን ከሃገር ሃገር በማሸጋገር አድራጎት ላይ ተሠማርቶ የነበረ ግለሰብ እርሷን፣ እናቷንና ወንድሟን በአይሮፕላን አሣፍሮ ወደ ኢንዶኔዥያ ላካቸው - በዚያ እነ ራና ማንንም የማያውቁ፣ የሃገሬውን አፍ የማይናገሩ ፍፁም ባይተዋር ናቸው።
አንድ ዓመት ኖሩና የስደተኛ ዕውቅና ተሰጣቸው። በፓሳር ሚንጉ ባሩ ሠፈርም ሕይወታቸውን አሣርፈው መሠረቱ ...
ለሙሉው ታሪክ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ