በዲሞክራክቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመንግሥት እና ኤም 23 በተሰኘው ታጣቂ ቡድን መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም፣ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ አባል ሀገራት አመራሮች ጥሪ አቅርበዋል።
በአካባቢው የሚገኙ የረድኤት ተቋማት ግጭቱ በቀጠናው ቀድሞውንም አስከፊ የነበረውን እና ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን ሰብዓዊ ቀውስ የበለጠ እያባባሰው ነው ብለዋል።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ረቡዕ ምሽት በድረ ገፅ አማካኝነት በመሩት ስብሰባ ላይ የሰባት አባል ሀገራት መሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ የኮንጎው ፕሬዝዳንት ፊሊክስ ቲሺሴኬዲ ግን በስብሰባ ሳይሳተፉ ቀርተዋል።
ስብሰባውን ተከትሎ መሪዎቹ ባወጡት መግለጫ፣ ተፋላሚዎቹ በምስራቅ ኮንጎ የሚካሄደውን ጦርነት እንዲያቆሙ እና የተጎዱ አካባቢዎች ለሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን እንዲያመቻቹ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም በዚህ ሳምንት በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ለኤም 23 አማፂያን ቡድን ያደላሉ ተብለው በሚገመቱ የበርካታ ሀገራት ኤምባሲዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መካሄዳቸው ተከትሎ፣ የኮንጎ መንግስት ሀገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች ጥበቃ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የኮንጎ መንግሥት ሩዋንዳ በዚህ ሳምንት ጎማ ከተማን የተቆጣጠረውን ኤም 23 ቡድን ትደግፋለች ሲል ይከሳል። በመሆኑም በቲሺሴኬዲ እና በካጋሜ መካከል የቀጠለው ፀብ ተኩስ እንዲቆም የሚደረገው ጥሪ እንዳይሳካ ሊያደርገው ይችላል ሲሉ ተንታኞች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለበርካታ አስርት አመታት በዘለቀ ቀውስ ውስጥ የቆየች ሲሆን በቀውሱ ምክንያት ከስድስት ሚሊየን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የሰብዓዊ ተቋማት አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም