በደቡብ አፍሪካ ለ30 ዓመታት በገዢ ፓርቲነት የቆየው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) በፓርላማው በበላይነት እንደማይቀጥል ቀድመው የወጡ የምርጫ ውጤቶች በማመልከት ላይ ናቸው። የትላንቱ የደቡብ አፍሪካ ምርጫ ከአፓርታይድ አገዛዝ ፍጻሜ ወዲህ የፖለቲካ ለውጥን ያስከተለ ምርጫ እንደሆነ በመነገር ላይ ነው።
አስራ ስድስት ከመቶ ከሆኑት የምርጫ ጣቢያዎች የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው፣ ኤኤንሲ 42.6 በመቶ ድምፅ ሲያገኝ፣ ‘ዲሞክራቲክ አላያንስ’ የተባለው ፓርቲ ደግሞ 25.8 በመቶ አግኝቷል። ‘ማርክሲስት ኢክኖሚክ ፍሪደም’ የተሰኘው ፓርቲ ደግሞ 8.5 በመቶ እንዳገኘ ከምርጫ ኮሚሽኑ የወጡ አሃዞች ያመለክታሉ።
በቅድሚያ እየወጡ ያሉት ውጤቶች፣ የመጨረሻውንም ውጤት የሚወክሉ ከሆነ፣ ኤኤንሲ ከአንድ ወይም ከአንድ በላይ ፓርቲዎች ጋራ በጋራ መንግስት ለመመሥረት ሊገደድ ይችላል ተብሏል። ይህም በመጪዎቹ ሣምንታት እና ወራት ከዚህ በፊት ያልታየ ፖለቲካዊ ትርምስ ሊፈጥር ይችላል ተብሏል።
ኤኤንሲ እንደ ከዚህ ቀደሙ እንደሻው እንዳይሆን የሚያደርግ ሲሆን፣ የውስጥ ፖለቲካ ሽኩቻው የመንግስት አስተዳደር ውጤታማ እንዳይሆን ሊያደርግ እንደሚችል ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው።
በደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት መሠረት አዲስ የሚቋቋመው ሸንጎ ፕሬዝደንቱን ይመርጣል። ኤኤንሲ አሁንም አብላጫ መቀመጫ ያለው ፓርቲ ሊሆን ስለሚችል፣ መሪው ሰሪል ራማፎሳ የሃገሪቱ ፕሬዝደንት ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ።
በክዋዙሉ-ናታል የቀድሞው ፕሬዝደንት ጄከብ ዙማ ያቋቋሙት አዲስ ፓርቲ፣ ከፍተኛ ድምፅን በማኘት ላይ ነው ተብሏል። የዙማ ፓርቲ እስከ አሁን ከተቆጠረው ድምፅ 42.7 በመቶውን ሲያገኝ፣ ኤ ኤን ሲ ደግሞ 21.4 በመቶ እንዳገኘ ተነግሯል።
በሕጉ መሠረት የምርጫ ኮሚሽኑ በሰባት ቀናት ውስጥ ውጤቱን ያሳውቃል።
መድረክ / ፎረም