በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኻሪስ እና ትራምፕ የሚፋለሙበት የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት በመራጮች እጅ ነው


መራጮች ኒውዮርክ በሚገኘው በብሮንክስ ካውንቲ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድምፃቸውን ሰጥተዋል፤ እአአ ኅዳር 5/2024
መራጮች ኒውዮርክ በሚገኘው በብሮንክስ ካውንቲ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድምፃቸውን ሰጥተዋል፤ እአአ ኅዳር 5/2024

በሚልየን የሚቆጠሩ የአሜሪካ መራጮች፣ ቀጣይ የአሜሪካ መሪ የሚሆኑት ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ኻሪስ ወይም የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መሆናቸውን ለመወሰን ዛሬ ማክሰኞ ድምፅ ይሰጣሉ።

እስከምርጫው ቀን ድረስ ከሕዝብ የተሰበሰቡ አስተያየቶች፣ በተለይ ከፍተኛ ፉክክር ይደረግባቸዋል ተብለው በሚጠበቁት እና አሸናፊውን ለመለየት ቁልፍ ሚና ባላቸው ግዛቶች፣ በእጩዎቹ መካከል ያለው ልዩነት እጅግ ጠባብ መሆኑን ያሳያሉ።

ትላንት ሰኞ ሁለቱም እጩዎች ከፍተኛ ትኩረት ወደሚደረግበት ፔንሴልቫኒያ ግዛት አምርተው ተከታታይ ሰልፎችን ያካሄዱ ሲሆን፣ በፒትስበርግ ከተማ አካባቢ ጎን ለጎን ያካሄዱት ሰልፍ በራሳቸው ዘመቻ ላይ ያላቸውን እምነት ያንፀባረቀ ነበር።

ፒትስበርግን የሀገሪቱ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ማዕከል ያደረገውን ትልቅ ለውጥ ባስተናገደው ታሪካዊ ስፍራ ላይ "ነገ የምርጫ ቀን ነው። ወደ ግባችን የሚያደርሰን ጥንካሬም ከኛ ጋር ነው" ሲሉ ንግግር ያደረጉት ኻሪስ፣ "ዘመቻችን የአሜሪካን ህዝብ ምኞት እና ህልም ያዘለ ነው። አሁን ጊዜው በአሜሪካ አዲሱ ትውልድ ወደ አመራር ቦታ የሚመጣበት ነው" ሲሉ ገልጸዋል። ኻሪስ አክለው "አጨራረሳችንም ጠንካራ መሆን አለበት" ያሉ ሲሆን "እንዳትሳሳቱ፣ እናሸንፋለን" ሲሉ ተናግረዋል።

የዴሞክራቲክ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በፒትስበርግ በተካሄደው ዘመቻ ላይ ንግግር አድርገዋል ፒትስበርግ፣ እአአ ኅዳር 4/2024
የዴሞክራቲክ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በፒትስበርግ በተካሄደው ዘመቻ ላይ ንግግር አድርገዋል ፒትስበርግ፣ እአአ ኅዳር 4/2024

በስታዲየም ውስጥ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ያደረጉት ትራምፕ በበኩላቸው፣ የትራምፕ አስተዳደር በድጋሚ ስልጣን ከተረከበ "በዓለም ታይቶ የማይታወቅ ልዩ የኢኮኖሚ እድገት እናስነሳለን" ብለዋል። "ለካማላ ከመረጣችሁ ሌላ ተጨማሪ አራት የመከራ፣ ውድቀት እና ጥፋት አመታት ይገጥማችኃል" ያሉት ትራምፕ "አገራችን ከዛ ላታገግም ትችላለች። ስለዚህ ድምፃችሁን ለኔ ስጡና ለእያንዳንዱ ዘር፣ ቀለም እና እምነት የደሞዝ ጭማሪ፣ የሚያድግ ገቢ፣ ከፍተኛ የስራ እድል፣ ሀብት እና እድል አመጣለሁ። ለእያንዳንዳቸው!"

ከማክሰኞው ምርጫ በፊት ከ81 ሚሊየን በላይ አሜሪካውያን በምርጫ ጣቢያዎች በአካል ተገኝተው ወይም በፖስታ ድምፃቸውን ሰጥተዋል። ይህ ቁጥር እ.አ.አ በ2020 ባይደን ትራምፕን ባሸነፉበት ምርጫ ድምፃቸውን ከሰጡት 158 ሚሊየን ሰዎች ከግማሽ በላይ የሚሆን ነው። በወቅቱ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ቢያሸንፍም፣ ትራምፕ እስካሁን ድረስ በድምፅ አሰጣጥ ሕጎች እና በድምፅ ቆጠራ የተጭበረበረ መሆኑን ይናገራሉ።

ትራምፕ የ2020ዎን ምርጫ ውጤት ተቃውመው ወደ ፍርድቤት ቢሄዱም የሾሟቸው ዳኞች ያሳለፉትን ጨምሮ፣ በርካታ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ከሳቸው የተቃረኑ ነበሩ። ሆኖም እሁድ በፔንሲልቫኒያ ለነበሩ ሰልፈኞች እ.አ.አ በ2021 ባይደን ስልጣን ሲረከቡ ዋይት ኃውስን "ጥዬ መውጣት አልነበረብኝም" ብለዋል።

ትራምፕ ዛሬ ማክሰኞ የሚካሄደውን ምርጫ ውጤት የሚቀበሉት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መካሄዱን ካረጋገጡ ብቻ ነው ያሉ ሲሆን፣ የዲሞክራት ተቺዎች በበኩላቸው "እሳቸው ካሸነፉ ብቻ" ማለታቸው ነው ብለው እንደሚገምቱ ገልጸዋል።

ማክሰኞ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ እየተገባደደ ሲሄድ፣ ማምሻውን እና በመጪዎቹ ቀናት አሸናፊው እስከሚታወቅ ድረስ የድምፅ አሰጣጥ እና የድምፅ ቆጠራ ሂደቶች ላይ በሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመገዳደር፣ የትራምፕ እና የኻሪስ ዘመቻዎች በርካታ ጠበቆችን ያካተተ ቡድን አቋቁመዋል።

የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በቫን አንዴል አሬና ግራንድ ራፒድስ፣ ሚች ውስጥ በተካሄደው ዘመቻ ላይ እአአ ኅዳር 5/2024
የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በቫን አንዴል አሬና ግራንድ ራፒድስ፣ ሚች ውስጥ በተካሄደው ዘመቻ ላይ እአአ ኅዳር 5/2024

ትራምፕ በዚህ ምርጫ ካሸነፉ፣ እ.አ.አ በ1880ዎቹ 22ኛው እና 24ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ካገለገሉት ግሮቭ ክሊቭላንድ ቀጥሎ፣ ሁለት ተከታታይ ያልሆኑ ግዜያትን ያገለገሉ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ይሆናሉ። ትራምፕ እ.አ.አ በ2016 ለፕሬዝዳንትነት ከመወዳደራቸው በፊትም አንዲት የወሲብ ፊልም ተዋናይትን ዝም ለማሰኘት ገንዘብ ከፍለዋል በሚል በቀረበባቸው 34 ክሶች ጥፋተኛ የተባሉ በመሆናቸውም፣ የቅጣት ውሳኔ እየጠበቁ ፕሬዝዳንት የሆኑ የመጀመሪያው በወንጀል ተጠያቂ ይሆናሉ።

ትራምፕ በምርጫ ዘመቻዎቻቸው ላይ ዲሞክራቲክ ተቀናቃኞቻቸውን "የሀገር ውስጥ ጠላቶች" እና የሀገሪቱ የወደፊት ስጋት ሲሉም ይተቿቸዋል። ኻሪስንም የማሰብ ችሎታቸው የተገደበ እና በዓለም አቀፍ ግንኙነቶቻቸው የሌሎች ሀገራት መሪዎች አሻንጉሊት እንደሚሆኑም ይናገራሉ።

ለሳምንታት ኻሪስ የማሸነፍ እድላቸው አነስተኛ እንደሆነ አርገው ሲናገሩ የቆዩ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሀገሪቱ 47ኛ ፕሬዝዳንት ሊሆኑ እንደሚችሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል። ኻሪስ ከተመረጡ፣ የመጀመሪያዋ ሴት አሜሪካዊ መሪ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ የመጀመሪያዋ በትውልድ ደቡብ እስያዊ እና ከባራክ ኦባማ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ጥቁር ፕሬዝዳንትም ይሆናሉ።

ኻሪስ ትራምፕን "ቁምነገር የሌላቸው" በማለት ለአሜሪካ ዲሞክራሲ ጠንቅ እንደሚሆኑ እና ከአንድ ፕሬዝዳንት ከሚጠበቁ ምግባሮች አንፃር ጤናማ አስተሳሰብ እንደሌላቸውም ይገልጻሉ።

የሕዝብ አስተያየቶች የአሜሪካ መራጮች በሁለቱ እጩዎች መካከል በከፍተኛ ሁኔታ የተከፋፈሉ መሆናቸውን ነው የሚያሳዩት። ይህም ዋና ዋና የሚዲያ ተቋማት ከዋናው የምርጫ ቀን ቀደም ብሎ ውጤቱን በሚመለከቱበት መንገድ ላይም የተንፀባረቀ ነው።

በቅርብ የተሰበሰቡ አስተያየቶችም የኻሪስ እና የትራምፕ ፉክክር በተለይ ከፍተኛ ትኩረት በሚደረግባቸው ግዛቶች በጣም የተቀራረበ ውጤት እንዳለው ያሳያሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG