በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የምሥራቅ አፍሪካ ጦር በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ‘ሠላም ሊያስከብር’ ነው


የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ
የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ

የኤም23 ታጣቂ ቡድን ጥቃት በከፈተባት በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምሥራቅ አፍሪካ ጦር ‘ሠላም ለማስከበር’ ይሰማራል ሲሉ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ዛሬ አስታውቀዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ጦር አካል የሆኑ የኬንያ ሠራዊት አባላት ከሣምንት በፊት ሁከት ወደሰፈነባት ምሥራቅ ኮንጎ አቅንተዋል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ ሆነው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሩቶ እንዳሉት የቀጠናው ጦር “ሁከትን ለመፍጠር ቆርጠው በተነሱ ሃይሎች ላይ” ሠላምን ለማስከበር እርምጃ ይወስዳል።

በአብዛኛው በኮንጎ ቱትሲ ሚሊሺያ የተዋቀረው ኤም 23 የተሰኘው አማጺ ሃይል በሰሜን ኪቩ ግዛት ሰፊ ቦታዎችን የተቆጣጠረ ሲሆን ጎማ ወደተባለችው ሌላዋ የኮንጎ ትልቅ ከተማ እየተጠጋ መሆኑ ተሰምቷል።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትንሿ ጎረቤቷ የሆነችውን ሩዋንዳ የኤም 23 ጦርን ትረዳለች ብላ በመወንጀሏ አካባቢያዊ ውጥረት ሰፍኗል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎችም ሩዋንዳ አማጺያኑን መደገፏን ደርሰንበታል ይላሉ።

ውንጀላውን በማስተባበል በሩዋንዳው የዘር ፍጅት ማግስት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተመሠረተን አንድ የሁቱ አማጺ ቡድን ትረዳለች ስትል ኪንሻሳን መልሳ ትከሳለች።

የኤም 23 አማጺ ቡድን ከ10 ዓመት በፊት ጎማን ለጥቂት ግዜያት ሲቆጣጠር ተሰሚነት አግኝቶ ነበር። ወዲያ በመጠቃቱ ግን አፈግፍጎና ተደብቆ ቆይቶ ነበር።

ተዋጊዎቼ በስምምነቱ መሠረት ወደ ዋናው የሃገሪቱ ጦር አልተቀላቀሉም በሚልና ሌሎች ቅሬታዎች ምክንያት አማጺያኑ ባለፈው ዓመት ተመልሰው ብቅ ብለዋል።

ኬንያ 900 የሚሆን ጦሯን ከምሥራቅ አፍሪካ ልዑክ ጋር በመሆነ ሠላም እንዲያስከብር ልካለች።

ሩቶ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ሞኑስኮ የተሰነው በሺህ የሚቆጠር የተመድ ሰላም አስከባሪ ሃይል በዲ.ሪ ኮንጎ የሚገኝ ቢሆንም፣ የምሥራቅ አፍሪቃ ጦር በለጠ ሃይል ይኖረዋል ብለዋል።

ሰባት አገራት ዓባል የሆኑበት የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ስብስብ ዛሬ የሰላም ጉባኤውን በኬንያ መዲና ናይሮቢ ያደርጋል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም፣ የንግግሩ መጀመሪያው ቀን አሁንም ግልጽ አይደለም።

ተመድ ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው እስከ አሁን ቢያንስ 262 ሺህ ሰዎች በግጭቱ ሳቢያ ተፈናቅለዋል።

ኤም 23 የተባለው አማጺ ቡድን በምሥራቅ ኮንጎ ከሚገኙ 120 አማጺ ቡድኖች አንዱ ነው።

XS
SM
MD
LG