በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጦር ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው ኢትዮጵያዊ በኔዘርላንድ የሚገኝ ፍ/ቤት ይግባኙን ውድቅ አደረገ


በኔዘርላንድ የሚገኝ የይግባኝ ፍ/ቤት እ.አ.አ በ2017 ዓ.ም በጦር ወንጀለኝነት ጥፋተኛ የተባሉትን ኢትዮጵያዊ አቶ እሸቱ ዓለሙን የዕድሜ ልክ እስራት ትናንት ረቡዕ አጽንቷል። የ67 ዓመቱ ተከሳሽ በኢትዮጵያ በ1960 ዎቹ እና በ1970ዎቹ በነበረው ጨካኝ ኮሚኒስት ሥርዓት ወቅት የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ሲል በደች የሚገኝ ፍ/ቤት የጥፋተኝነት ብይን ከአምስት አመታት በፊት ሰጥቶ ነበር።

አቶ እሸቱ ዓለሙ የ2017 ፍርድ እንዲቀለበስላቸው ይግባኝ ጠይቀው የነበረ ቢሆንም በሄግ የሚገኘው የይግባኝ ፍ/ቤት ግን በ1960ዎቹ መጨረሻና በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ በመንግሥቱ ኃይለማሪያም አመራር በተፈጸመው የቀይ ሽብር ዘመቻ ተሳታፊ ነበሩ ሲል ውሳኔውን አጽንቷል። አቶ እሸቱ በመታመማቸው ምክንያት በይግባኝ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል።

አንዳንድ የጉዳዩ ባለሞያዎች እንደሚሉት ወደ 150,000 የሚጠጉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ምሑራንና የፖለቲካ ሰዎች በወቅቱ የነበረው ስርዓት ተቃዋሚዎቹን ለማጥፋት ባደረገው ዘመቻ በጭካኔ ተገድልዋል። የሂውማን ራይትስ ዎች በበኩሉ የቀይ ሸብሩን ዘመቻ “በአፍሪካ በመንግስት የተፈጸመ ስልታዊ የጅምላ ግድያ” ሲል ይገልጸዋል።

አቶ ዓለሙ እአአ በ1978 በጎጃም ክፍለ ሀገር የደርግ ተወካይ የነበሩ ሲሆን፣ በወቅቱ ደርግ በክፍለ ሀገሩ ከተቃዋሚዎቹ አንዱ ከነበረው ከኢህአፓ ጋር ሲፋለም ነበር።

ፍ/ቤቱ እንዳለው “በተከሳሹ እውቅናና ተሳትፎ” የጦር ወንጀል በክፍለ ሃገሩ ይፈጸም ነበር።

በእንግሊዝኛ በተጻፈው የይግባኝ ፍ/ቤቱ ውሳኔ ጭማቂ መሰረት በመቶዎች የሚቆጠሩና አብዛኞቹ ወጣት ተማሪዎች የሆኑት ሰለባዎች ካለ በቂ ምክንያት ተይዘው ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ የታሰሩ ነበር።

አንዳንዶች በከፋ ሁኔታ ሲደበደቡ አብዛኞቹ ደግሞ ካለ ፍርድ ሂደት ወደ እስር ቤት ይጋዙ ነበር። በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰለባዎች ደግሞ በሞት ተቀጥተዋል።

“የሞት ቅጣቱ በተከሳሹ አመራር ሰጪነት በጭካኔ ይፈጸም ነበር” ብሏል ፍ/ቤቱ።

አቶ ዓለሙ በ2017 የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠበት የፍርድ ሂደቱ መጀመሪያ ላይ በስሜት ተሞልቶ ባደረገው ንግግር በደርግ ላይ የቀረበውን ውንጀላ ተቀብሎ ነገር ግን እርሱ በግሉ የፈጸማቸው አለመሆናቸውን ለዳኞች ገልጾ ነበር።

አቶ ዓለሙ በደች ፍ/ቤት ጉዳያቸው ሊታይ የቻለው ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ጀምሮ ኔዘርላንድ ውስጥ መኖር በመጀመራቸውና በ1998 የሀገሪቱን ዜግነት በመቀበላቸው ነው።

ኮሎኔል መንግስቱ አሁን በዚምባብዌ ሲገኙ፣ የሃገሪቱ ፍ/ቤት እአአ በ2006 በዘር ማጥፋት ወንጀል የጥፋተኝነት ብይን ሲሰጥ፣ በኋላም በሌሉበት የሞት ፍርድ ወስኖባቸዋል።

ዘገባው የአሶስዬትድ ፕሬስ ነው

XS
SM
MD
LG