በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኤም 23 አማጺያን የጎማን አብዛኛውን ክፍል ተቆጣጠሩ


በኤም 23 አማጺያን እና በየኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በተነሳ ግጭት በጎማ ጎዳናዎች ላይ የተጣሉ ወታደራዊ ልብሶች እና ቁሳቁሶች፤ ጎማ፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እአአ ጥር 29/2025
በኤም 23 አማጺያን እና በየኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በተነሳ ግጭት በጎማ ጎዳናዎች ላይ የተጣሉ ወታደራዊ ልብሶች እና ቁሳቁሶች፤ ጎማ፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እአአ ጥር 29/2025

በሩዋንዳ የሚደገፉት የኤም 23 አማጺያን የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ምሥራቃዊ ከተማ ጎማን ሙሉ ለሙሉ በሚባልና አየር ማረፊያውን መቆጣጠራቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

ከከተማዋ በርካታ ነዋሪዎች ለቀው መውጣታቸው ሲታወቅ፣ አንድ ሚሊዮን ሠዎች በሚኖሩባት ጎማ የሚገኙ ነዋሪዎች ቀስ በቀስ ከቤታቸው መውጣት ጀምረዋል። አንዳንዶቹም "ዛሬ ፍርሃት ለቆናል" ሲሉ ተደምጠዋል። ነገር ግን ረሃብ እንደገባ፣ ውሃና መድሃኒት ማግኘት እንዳለባቸው እንዳንዶቹ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በከተማዋ በሦስት ቀናት ውስጥ 100 ሰዎች ሲገደሉ 1 ሺሕ የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል። አብዛኞቹ አስከሬኖች ከመንገድ ላይ አሁንም እንዳልተነሱ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የተደረገው ውጊያ ወትሮውንም የነበረውን ሰብአዊ ቀውስ እንዳባባሰ ተመልክቷል። የምግብና የውሃ እጥረት ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ መኖሪያውን ለቆ እንዲወጣ አስገድዷል።

የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ፊሊክስ ቺሰኬዲ ዛሬ ከሩዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ጋራ ሊደረግ በነበረው የሠላም ስምምነት ላይ እንደማይገኙ አስታውቀዋል። ፕሬዝደንቱ ዛሬ ለሃገራቸው ሕዝብ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ አሜሪካ በኮንጎ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እንደምትሻ ለሩዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ እንደነገሯቸው አስታውቀዋል።

ፖል ካጋሜ በበኩላቸው የተኩስ አቁም በሚደረግበትና የግጭቱን መነሻ ምክንያት በተመለከተ መፍትሄ በሚሰጥበት ጉዳይ ላይ ከአዲሱ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋራ መነጋገራቸውን አስታውቀዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG