ዋሺንግተን ዲሲ —
የኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፖብሊክ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ በመጪው እኤአ ታህሳስ 23 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ገለጹ። የወደፊት የፖለቲካ ዕቅዳቸውን አልተናገሩም።
ካቢላ ትናንት በቴለቪዥን ለህዝቡ ባደረጉት ንግግር ህገ መንግሥቱን ያለምንም ማወላወል አከብራለሁ ብለዋል። ተቃዋሚዎች ግን ፕሬዚዳንቱ መንበረ ሥልጣኑን የሙጥኝ ይሉ ይሆናል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልፀዋል።
የሚስተር ካቢላ የሁለት የሥልጣን ዘመን ገደብ ካለቀ ሁለት ዓመት ሆኖታል። ይሁን እንጂ በሁከቱ በታጣቂ ሚሊሺያዎችና ምርጫ ለማደራጀት በገጠሙ ችግሮች ሳቢያ አዲስ ምርጫ ሁለት ጊዜ እንዲዘገይ ተደርጓል።
ህገ መንግሥቱም ካቢላ ተተኪ እስከሚመረጥ ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ይፈቅድላቸዋል። ተቃዋሚዎችና ዩናይትድ ስቴትስ ሌሎችም ጭምር በምርጫዎቹ መዘግየት ማዘናቸውን ገልፀዋል። ካቢላ በትናንቱ ንግግራቸው ኮንጎ ስለዲሞክራሲ ማንም እንዲያስተምራት አትፈልግም ብለዋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ