በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የልብ ሐኪሙ የዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ጉዳይ


ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ /ፎቶ - ከኢንተርኔት የተገኘ/
ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ /ፎቶ - ከኢንተርኔት የተገኘ/

ዶ/ር ፍቅሩ ማሩና ሌሎችም ከሙስና ጋር በተያያዙ ክሦች እሥር ቤት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ጉዳይ ለፊታችን ማክሰኞ፤ ጥቅምት 9/2008 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡ ጠበቆቻቸው ደንበኛቸው የተከሰሱበት መዝገብ አብረዋቸው ከተከሰሱት ሰዎች ጉዳይ ጋር የሚገናኝ ባለመሆኑ ተነጥሎ እንዲወጣና እንዲታይ እየጠየቁ ነው፡፡

የልብ ሐኪሙ የዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ጉዳይ /ድምፅ mp3- ርዝመት 30ደ16ሰ፤ መጠን 27.7ሜባ/
please wait

No media source currently available

0:00 0:30:16 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

ዶ/ር ፍቅሩ ማሩና ሌሎችም ከሙስና ጋር በተያያዙ ክሦች እሥር ቤት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ጉዳይ ለፊታችን ማክሰኞ፤ ጥቅምት 9/2008 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡

ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ /ፎቶ - ከኢንተርኔት የተገኘ/
ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ /ፎቶ - ከኢንተርኔት የተገኘ/

የዶ/ር ፍቅሩ ጠበቆች ደንበኛቸው የተከሰሱበት መዝገብ አብረዋቸው ከተከሰሱት ሰዎች ጉዳይ ጋር የሚገናኝ ባለመሆኑ ተነጥሎ እንዲወጣና እንዲታይ እየጠየቁ ነው፡፡

ከጠበቆቻቸው አንደኛው አቶ አበበ እሸቱ ለቪኦኤ በሰጡት ማብራሪያ ዶ/ር ፍቅሩ የተከሰሱት የሕክምና መገልገያዎችን ከውጭ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሊያስገቡ ሞክረዋል በሚል እና ተያይዞም የተነሣውን ክርክር ለማስዘጋት መደለያ ሰጥተዋል በሚል እንደነበረ ገልፀው ይሁን እንጂ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ በተመሠረተባቸው ክሥ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ለፍርድ ቤት በሰጡት የዕምነት ክህደት ቃል ተናግረው እየተከራከሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም የተከሰሱበት ሕግ እርሣቸው ከተያዙ በኋላ በወጣ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 መለወጡንና እርሣቸው ‘ፈፅመዋል’ የተባለውን ጥፋት ከወንጀል ወደ አስተዳደራዊ ጉዳይነት የለወጠው መሆኑን አቶ አበበ እሸቱ ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ክሡ “ከእነ …” ዶሴ እንዲወጣ ብቻ ሣይሆን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 22 በሚፈቅደው መሠረት አዲሱ ሕግ ደንበኛቸውን ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ስለሚያግዛቸው ፍርድ ቤቱን እየጠየቁ ያሉት ውድቅ እንዲደረግና በነፃ እንዲሰናበቱም መሆኑን ጠበቃቸው አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ “አዲስ የልብ ሕክምና ማዕከል”ን ሲያቋቋሙ ያገዟቸው ስዊድን ውስጥ የሆስፒታል ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲ መምሕር የሆኑት የልብ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ፕሮፌሰር ዊክለንድ ላርስ ዶ/ር ፍቅሩ ወደ ኢትዮጵያ ሊያስገቧቸው ሞክረዋል የተባሉት ቁሣቁስ አሮጌና እራሳቸው ከስዊድን ሆስፒታሎች በእርዳታ ያሰቧሰቧቸው ዋጋቸው ርካሽ የሆነ ክፍት የልብ ቀዶ ሕክምና በሚሠራበት ጊዜ ድጋፍ ሰጭ የሆኑ ብልቃጦች /ትዩቦች/ መሆናቸውን ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ በሚሰጡት የልብ ምትን በሚያስተካክል የልብ ቀዶ ሕክምና ዓይነት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው ባለሙያ መሆናቸውንና በእርሣቸው ምክንያትም ብዙ የሕክምናው ፈላጊዎች ወደ ውጭ ከመጓዝ፣ ከመንገላታትና የውጭ ምንዛሪ ከማፈላለግ እፎይታን አግኝተው እንደነበረ የሆስፒታሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሙላቱ ሲሣይ ገልፀዋል፡፡

የግል ሆስፒታሎች ማኅበርም ለኢፌዴሪ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በፃፈው ደብዳቤ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ጉዳያቸው በፍርድ እየታየም ቢሆን ቢያንስ የእርሣቸውን ሙያ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው ጠይቋል፡፡

ከዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ጋር የሠሩት ፈረንሣይ ውስጥ የሚገኙ ስዊድናዊት ሐኪም ዶ/ር አኒካ ስማርስ ደግሞ ዶ/ር ፍቅሩ መደለያ ሰጡ ይባል እንጂ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩን አመልክተው እርሣቸው እስከሚያውቋቸው “…ዶ/ር ፍቅሩ መደለያ የሚባልን ነገር አጥብቀው የሚጠሉ ወይም የሚፀየፉ ሰው ናቸው…” ብለዋቸዋል፡፡

ስለጉዳዩ ከቪኦኤ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት የኢትዮጵያ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌይማን የግል ሆስፒታሎች ማኅበር ደብዳቤ እንዳልደረሣቸው ተናግረው በሕግ በተያዘ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ገልፀዋል፡፡

ለሙሉው ዘገባ ከላይ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG