ሶማሊያ በበርካታ አሰርት ዓመታት ባልታየ ድርቅ በተጎዳችበት በአሁኑ ወቅት የሚሰጣት ሰብዓዊ ዕርዳታ ሊቀነስባት እንደሚችል የጠቆሙ የሃገሪቱ የዕርዳታ ሠራተኞች ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው አስታወቁ።
የለጋሾች መሰላቸት እና በዓለም ዙሪያ ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ቀውሶች ስላሉ ሶማሊያ የምታገኘው ሰብዓዊ ድጋፍ መጠን ሊቀንስባት እንደሚችል የረድኤት ሰራተኞቹ ሰግተዋል።
በቅርቡ የሶማሊያ መንግሥት እና የሰብዓዊ ረድዔት ድርጅቶች በዚህ እአአ 2023 በሶማሊያ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎችን ለመርዳት የሚውል 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መማጸናቸው ይታወሳል።
በመጪው የመጸው ወቅት በቂ ዝናብ ካልጣለ እና የሰብዓዊ ረድዔት ድጋፉ ካልቀጠለ ከባድ ቸነፈር ሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት አሰምተዋል።