በጂቡቲ የፓርላማ ምርጫ ገዢው ፓርቲ እንደተጠበቀው ከፍተኛውን መቀመጫ መያዙን የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ለኤ.ኤፍ.ፒ አስታውቀዋል።
ባለፈው ዓርብ በተደረገው ምርጫ ዋና ዋናዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሂደቱ የተጭበረበረ ነው በሚል ሳይሳተፉ ቀርተዋል።
በፓርላማው 65 መቀመጫዎች ሲኖሩ፣ ግዜያዊ የምርጫ ውጤት እንደሚያሳየው “አንድነት ለፕሬዚዳንታዊ አብላጫ ድምጽ” የተሰኘው ገዢ ፓርቲ 58 መቀመጫዎችን ማሸነፉን አገሪቱን ከ23 ዓመታት በላይ ያስተዳደሩት ፕሬዚዳንት ኦማር ገሌ አማካሪ የሆኑት አሌክሲስ ሞሃመድ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።
ቀሪዎቹን ሰባት መቀመጫዎች ሌላው ብቸኛ ተወዳዳሪ የሆነው አንድነት ለዲሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ ማሸነፉን አማካሪው ይፋ አድርገዋል።
በውጤቱ ገዢው ፓርቲ ከ5 ዓመታት በፊት በተደረገው ምርጫ የያዛውን የመቀመጫ ብዛት መልሶ አግኝቷል።
230 ሺህ የሚሆኑ ጂቡቲያውያን ለመምረጥ ብቁ ቢሆኑም፣ በምርጫው ዕለት የታየው ድምጽ ሰጪ ቁጥር ዝቅተኛ ነው ተብሏል።
የ75 ዓመቱ ኦማር ገሌ የፕረስ ነጻነትንና የተቃዋሚን መብት ይጨፈልቃሉ የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል። ጂቡቲ ነጻነቷን ካገኘች ወዲህ ሁለተኛ ፕሬዚዳንት የሆኑት ገሌ በድጋሚ ለምርጫ አይሳተፉም፤ ምክንያቱም ህገ መንግሥቱ የፕሬዚዳንቱን ዕድሜ 75 ላይ አግዷል።