በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጂቡቲ መንግስት አርብለት የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ አከሸፈ


የጂቡቲ የተቃዋሚ መሪዎች በዛሬውለት በጁምዓ ጸሎት በኋላ ጠርተውት በነበረው የጸረ-መንግስት ተቃውሞ፤ ብዙ ህዝብ ሳይገኝ ቀረ።

ጂቡቲን ከ1991ዓም ጀምሮ ያስተዳደሩት ፕሬዝደንት ኦማር ጊሌ ከስልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቁ ተቃዋሚዎች ከሁለት ሳምነት በፊት ተመሳሳይ ትእይንተ-ህዝብ ማድረጋቸው አይዘነጋም።

ከሁለት ሳምንት በፊት በጂቡቲ መዲና ከ5-15ሽህ የተገመቱ ተቃዋሚዎችን ለጸረ-መንግስት ተቃውሞ ለማስወጣት እንደቻሉ የተናገሩት የጂቡቲ የተቃዋሚ መሪዎች፤ የዛሬው ጥሪያቸው ግን አልተሳካላቸውም።

ጂቡቲያዊያን ከአርብ ጸሎታቸው መልስ ፕሬዝደንት ኦማር ጊሌ ከስልጣን እንዲወርዱ በመጠየቅ የሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ ተቃዋሚዎች ያሳለፉት ጥሪ፤ በጥቂቶች ብቻ ነው ተሰሚነት ያገኘው።

ፕሬዝደንት ጊሌ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር እንዲያስችላቸው ከአንድ አመት በፊት ህገ-መንግስቱን መቀየራቸውን ተቃዋሚዎቹ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል።

የዛሬው ሰልፍ መንግስታዊ ፈቃድ እንደሌለው የጂቡቲ መንግስት አስቀድሞ ቢያስታውቅና ተቃዋሚዎች ጥሪያቸውን እንዲያነሱ ቢጠይቅም፤ የጸረ-መንግስት ሰልፎቹ እንደሚካሄዱ ነበር ተቃዋሚዎች ባቋማቸው የጸኑት። የተቃዋሚው መሪ አደን ሮብሌ ለቪኦኤ የሶማሊኛ ዝግጅት በሰጡት ቃል የሰላማዊ ሰልፉ ተካሂዷል ብለዋል።

“የተቃውሞ ሰልፉ ከሽፏል የሚለው ከውነት የራቀ ነው። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ለሁለት ኪሎሜትር በሚረዝም ሰልፍ በከተማዋ ጎዳናዎች ድምጻቸውን አሰምተዋል። በአንድ ስፍራ የጸጥታ ሀይሎች አስለቅሽ ጋዝ ሲተኩሱ የጦር ሰራዊቱም በዚያው ነበር።”

የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሃሙድ አሊ ዩሱፍ ሰላማዊ ሰልፍ አለመኖሩን ይናገራሉ።

“በመንግስቱ ስም የምገልጸው ነገር ቢኖር ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ አልተካሄደም። ህዝቡ የመንግስቱን ጥሪ ሰምቷል። ከቤታቸው አልወጡም። ተቃዋሚዎቹ እንደሚሉት እኛ ሰልፍ እንዳካሂዱ አላገድናቸውም። በጎዳና ላይ ያሰማራናቸው ጥቂት የመንግስት ሀይሎች ህዝቡ ገንፍሎ ከወጣ ይቋቋሙታል ብለን አናምንም። በመካከለኛው ምስራቅ የሆነውን ማስተዋል ይቻላል።”

በስፍራው የተገኘው የአሜሪካ ድምጽ ዘጋቢ የመንግስቱ ሃይሎች የሰላማዊ ሰፉ እንዳይካሄድ በተሳካ ሁኔታ መከልከሉንና ብዙ ሰዎች ለሰልፍ እንዳልወጡ አረጋግጧል።

XS
SM
MD
LG