በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊያ በጎርፍ በተጥለቀለቀችው ዶሎ በሽታ መቀስቀሱ ተገለጠ


ደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ የዶሎ ወረዳ ያጥለቀለቀው ጎርፍ ጎዳናውን ሞልቶት ይታያል
ደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ የዶሎ ወረዳ ያጥለቀለቀው ጎርፍ ጎዳናውን ሞልቶት ይታያል

የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያዋን የዶሎ ወረዳ ያጥለቀለቀው ጎርፍ መቀነስ ቢጀምርም፣ መኖሪያ ቤቶቻቸው በጎርፉ የሰመጡባቸውና እና መተዳደሪያቸውን በዚሁ አደጋ ያጡ ቤተሰቦች አሁን ደግሞ ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ በሽታዎች እንደተጋረጡባቸው ተዘገበ።

የሶስት ልጆች እናት የሆነችው የ34 ዓመቷ ሹክሪ አብዲ ኡስማን በከተማዋ በርካታ አካባቢዎች የደረሰውን የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከትሎ ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ ቁጥራቸው 700 የሚደርሱ ቤተሰቦች ከተጠለሉባት እዚያው ዶሎ ካለች ካምፕ ውስጥ ትገኛለች።

"ይህን መሰል ውድመት ያስከተለ ጎርፍ ካሁን ቀደም አይቼ አላውቅም። ጎርፉ መድረሱን በተረዳንበት ወቅት ንብረታችንን ለመሰብሰብ ጊዜ አልነበረም። መኖሪያ ቤታችንን ጥለን የወጣነው እኩለ ሌሊት ላይ ሲሆን፤ መያዝ የቻልነውም ልጆቻችን ብቻ ነበር" ስትል ሹክሪ ስለሁኔታው ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግራለች። አሁን ደግሞ በመጠለያ ካምፑ ውስጥ የተቀሰቀሰ በሽታ የቤተሰቧን ደህንነት አደጋ ላይ መጣሉን አመልክታለች።

"መጸዳጃ ቤቶች ወድመዋል። ሌላው ቀርቶ የቧንቧ ውሃ ሳይቀር ከጎርፉ እና ከቆሻሻ መውረጃ ከሚመጣው የተበከለ ፈሳሽ ጋር ተቀላቅሏል" ያለችው ሹክሪ፡ አያይዛም "በካምፑ ያለው ሁኔታ እጅግ የበረታ ነው፡፡ ሴቷ ልጄ ጤና ታማለች። ለወባ እና ለተስቦ በሽታዎች ሳትጋለጥ አትቀርም” ስትል አስረድታለች።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት "በክፍለ ዘመን አንዴ" የሚታይ ያለው የጎርፍ አደጋ፣ በመላዋ ሃገሪቱ ለ100 ያህል ሰዎች ህይወት መጥፋት እና ለ700 ሺሕ ሰዎች ቤት አልባነት ምክንያት መሆኑን ተከትሎ የሶማሊያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አውጇል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG