በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያና ጀርመን


የጀርመን የኢኮኖሚ ልማትና የትብብር ሚኒስትር ሚስተር ዲርክ ኒበል፡፡
የጀርመን የኢኮኖሚ ልማትና የትብብር ሚኒስትር ሚስተር ዲርክ ኒበል፡፡

የጀርመን የኢኮኖሚና የትብብር ሚኒስትር የኢትዮጵያ ቆይታና ውይይቶቻቸው፡፡

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉድለት መኖሩን ቢታዘቡም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የልማት ፍላጎት ያላት ሃገር መሆኗን ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የጀርመን የኢኮኖሚ ልማትና የትብብር ሚኒስትር አስታወቁ፡፡

ሚስተር ዲርኬ ኒበል በጉብኝታቸው ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውንና ኢትዮጵያ ከሃገራቸው ዋነኛ የትብብር አጋሮች አንዷ በመሆኗ ምክንያት ለልማቷ መጠናከር የበለጠ ለመሥራት እንደሚፈልጉ ከአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ፒተር ሃይን ላይን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ደግሞ የግሉ ዘርፍና ሲቪሉ ማኅበረሰብ በልማት እንቅስቃሴው ውስጥ የጎላ ሚና እንዲኖራቸው እንደሚፈልጉ ጠቅሰዋል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዱ "ኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ጉድለት እናያለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የልማት አቅጣጫን አጥብቀው ከያዙ የዓለም ሃገሮች አንዷ ነች፡፡ የራሣቸውን ጉዳይ በባለቤትነት ይዘዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ለመደራደር አስፈላጊ የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡" ብለዋል፡፡

የጠቀሱትን የዴሞክራሲ ጉድለት አስመልክቶም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጧቸው ማብራሪያ ይኖር እንደሆነ ሚስተር ኒብል ተጠይቀው በኢትዮጵያ ያለውን የምርጫ ሥርዓት ያስረዷቸው መሆኑንና "እያንዳንዱ ድምፅ እኩል ከሆነባት ሃገራቸው" የተለየ ሆኖ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

"መሬት መቀራመት" እየተባለ በልማድ በሚጠራው የመሬት ኪራይ ጉዳይ ላይ መወያየታቸውን ሚኒስትሩ ጠቁመው ገበሬዎች ሣይፈናቀሉ ግብርናውን እንደሚያለሙ ያረጋገጡላቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ስለሲቪል ማኅበራት፣ ስለግሉ የኢኮኖሚ ዘርፍ መጠናከርና መስፋፋት አስፈላጊነት፣ ስለሲቪል ማኅበራት ማቋቋሚያ ደንብና የውጭ ኢንቨስትመንት ጥበቃና እንክብካቤ፣ ስለጀርመንም የልማት ድጋፍና ገበያውን በማጠናከር በኩልም ሊጫወት ስለሚችለው ሚና፣ ሚስተር ዲርክ ኒብል ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር መወያየታቸውን አብራርተዋል፡፡"

"ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳች ነገር ለመለወጥ የምትፈልግ ከሆነ - አሉ ጀርመናዊው ሚኒስትር በዚህ ቃለምልልስ ወቅት - ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንተ ጎን እንዲቆሙ ያስፈልጋል፡፡"

ዝርዝሩን ከዘገባው ያድምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG