ደሴ ከተማ ውስጥ ተፈጠረ በተባለ የተኩስ ልውውጥ እና የቦንብ ፍንዳታ የአምስት ሰዎች መሞታቸውን የከተማዋ ፖሊስ ለአሜሪካ ድምፅ ገለፁ።
ትናንት ትጥቅ እንዲፈታ የታዘዘ ግለሰብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ በተፈጠረው አለመግባባት የግለሰቡና የሁለት ባልደረቦቹ፣ እንዲሁም የሁለት ፖሊሶች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታውቋል።
ትናንት የደሴ ከተማ ፖሊስ በወንጀል ይፈለጋል ያለውን ግለሰብ ለምርመራና ትጥቅ ለማስፈታት ሙከራ እያደረገ ሳለ ችግሩ እንደተፈጠረ የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አሳምነው ሙላት ገልጸዋል፡፡
በቦምብና በተኩስ ልውውጡ ፖሊስ ተፈላጊ ሲል የጠራው ግለሰብና ሁለት ግብረ አበሮቹ እንዲሁም በምርመራ ተግባር ላይ የነበሩ ሁለት ፖሊሶች በድመሩ አምስት ሰዎች ወዲያውኑ ሞተዋል፡፡ አንድ ሰው መቁሰሉንና የግለሰቡ አጃቢ እንደነበር የተነገረለት አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ ጠቅሷል፡፡ ኮማንደር አሳምነው “ግለሰቡ ተደጋጋሚ ወንጀሎችን ሲፈጽም ነበር” በማለት ይከሳሉ። ከዚህ በተጨማሪ በደሴ ከተማ በቅርቡ በሁለት ወርቅቤቶች ላይ በተፈጸመው ዘረፋ ላይ ግለሰቡ እንዳለበት ማረጋገጫ አለኝ ይላል ፖሊስ፡፡
አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ግን ግለሰቡ በዚህ ደረጃ ወንጀል ካለበት እንዴት እስካሁን ሳይያዝ ቆየ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ግለሰቡ የፋኖ አባል ነበር ሲሉ ፖሊስ በበኩሉ “ሕጋዊ ባልሆነ አደረጃጀት ራሱን ያስታጠቀ ነው” ሲል ገልጾታል፡፡
እስከ አስር ደቂቃ የሚደርስ የተኩስ ልውውጥ ከተደረገ በኋላ በከተማዋ ቧንቧ ውሃ አደባባይ አካባቢ ተሽከርከሪዎች ለሰዓተት እንዳይንቀሳቀሱ ታግደው ነበር፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተማዋ የሚሰሙ የተኩስ ልውውጦች የደህንነተ ሥጋት ፈጥሮብናል የሚሉ የከተማዋ ኗሪዎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
/ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/