ማሊ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ያያዘውን ወታደራዊ ኃይል በመደገፍ ትናንት ሰልፍ አድርገዋል። ሃገሪቱ ወደ ሲቪል አስተዳደር ስለምትመለስበት ጊዜ፣ ክርክር እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል።
እያቆጠቆጠ ያለውን የጂሓዳውያን እንቅስቃሴን፣ ደም ያፋሰሰ የዘር ግጭትንና ሙስናን በመቃወም፣ ለወራት ያህል ሰልፎች ሲካሄዱ ከቆዩ በኋላ፣ ያመጹ ወታደሮች ከ23 ቀናት በፊት የሀገሪቱን ፕሬዚዳንት አሰሩ።
ትናንት በመዲናይቱ ባማኮ የተካሄደውን ተቃውሞ ያስተባበረው፣ የሰኔ አምስት ንቅናቄ የሚል ስያሜ ያለውና የመስከረም 4 ህዝባዊ ንቅናቄ የተባለ አዲስ ቡድን ጥምረት መሆኑ ተገልጿል።
ወታደራዊው ኃይል ሥልጣን እንደያዘ፣ ምርጫ እንደሚካሄድ ቢገልጽም፣ ለሦስት ዓመታት ያህል በወታደራዊው ኃይል የሚመራ የሽግግር መንግሥት እንደሚኖር ተናግሮ ነበር። ወደ ኋላ ግን ወደ ሁለት ዓመታት እንዳወረደው ተዘግቧል።
ኢኳዋስ በሚል አህፅሮት የሚታወቀው፣ 15 ሃገራትን የሚያቅፈው የምዕራብ አፍሪካ ሃገሮች የኢኮኖሚ ማኅበረስብ ግን፣ የሽግግሩ ወቅት በሲቪል ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ተመርቶ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ጠይቋል።
ኢኳዋስ በመፈንቅለ መንግሥቱ ምክንያት፣ የድንበሮች መዘጋትንና የንግድ ዕገዳን ያካተቱ ማዕቀባቦች ማሊ ላይ ጥሏል። ሲቪል የሽግግር መንግሥት መሪዎች፣ እስከ መጪው ማክሰኞ ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲሰያሙ ጠይቋል።
ወታደራዊው መፈንቅለ መንግሥት ዓለምቀፍ ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ በሀገሪቱ በሚካሄደው ደም መፋሰስና የኢኮኖሚ መንገዳገድ በተሰላቹ አንዳንድ የሃገሪቱ ተወላጆች ግን፣ ድጋፍ ማግኘቱ አልቀረም።