በትናንትናው ዕለት ለ2ተኛ ቀን የተካሄደው የዴሞክራቲክ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ/ኮንቬንሽን የቀድሞ ም/ፕሬዚዳት ጆ ባይደንን የፓርቲው ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ አድርጎ በይፋ ሰይሟል፡፡ በድረ-ገጽ ወይም በኢንተርኔት በተካሄደው በዚህ ጉባኤ የጆባይደንን ባለቤት ጂል ባይደንን ጨምሮ ከዴሞክራቲክ እና ከሪፖብሊካን ፓርቲዎች የተጋበዙ እንግዶች ዕጩ ፕሬዚዳንቱን ጆ ባይደንን በመደገፍ ንግግር አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የቀድሞ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን፣ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሊን ፓወል ይገኙበታል፡፡
ጠቅላላው ጉባኤ በዛሬውም ዕለት ቀጥሎ የሚውል ሲሆን በዛሬው ዕለት የቀደሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች እንደሚናገሩ ይጠበቃል።
በትናንትናው ምሽት የማጣሪያ ምርጫዎችን መሠረት አድርገው ድምጽ የሚሰጡት የየአካባቢው ተወካዮች ሮሎ ኮል በሚባለው የድምጽ አሰጣጥ መሠረት ባይደንን በይፋ መምረጣቸውንና ድጋፋቸውንም የሚሰጧቸው መሆኑን በይፋ አሳውቋል፡፡
ዕጩነቱን የተቀበሉት ጆ ባይደንም “ለዚህ መመረጥ ማለት ለኔና ለቤተሰቤ ዓለም ነው፡፡ በመጭው ሀሙስ አያችኋለሁ” በማለት ዕጩነታቸውን በይፋ የሚቀበሉበትን ንግግር የሚያሰሙበትን የጠቅላላ ጉባኤውን የመጨረሻ ዕለት አስታውሰዋል፡፡ በዛሬው ረቡዕ ምሽት የዴሞክራቶቹ ጠቅላላ ጉባኤ ወይም ኮንቬሽን የሚቀጥል ሲሆን፣ የካሊፎኒያዋ ሴነተርና የዴሞክራቶቹ ም/ፕሬዚዳንት ዕጩ ከማላ ኸሪስ ዕጩነታቸውን የተቀበሉ መሆናቸውን በይፋ የሚያረጋግጡብትን ንግግር ያሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዴሞክራቶቹ በድረ-ገጽ ተሰብስበው ጉባኤያቸውን በሚያከበሩበት ወቅት የጆ ባይደን ተቀናቃኝ የሆኑት ፕሬዚዳንት ትረምፕ ብርቱ ፉክክር ይታይባቸዋል ወደሚባሉት አይዋ እና አሪዞና ክፍለ ግዛቶች አምርተዋል፡፡ በዚያም የሴቶችን ድጋፍ ለማግኘት በ1870 ሴቶች በምርጫ ተሳትፈው ድምጽ እንዳይሰጡ የተቀመጠውን ህግ በመጣስ ድምጽ የሰጠቸውን የሴቶች መብት ተሟጋች መሪ ሱዛን ቢን አንተኒን በማሰብ የሴቶችን ድጋፍ ለማግኘት ያቀዱ መሆኑም ተነግሯል፡፡