በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አራት የሕወሓት አመራሮች መገደላቸውን ዘጠኝ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መንግሥት አስታወቀ


ሴኩቱሬ ጌታቸው
ሴኩቱሬ ጌታቸው

የሕወሓት የቀድሞ አመራር አባል ሴኩቱሬ ጌታቸውን ጨምሮ አራት አመራሮች መገደላቸውን መንግሥት አስታወቀ። ከአንድ ወር በፊት በድምፀ ወያኔ የቴሌቭዥን ጣቢያ ላይ በነበራቸው ውይይት “የሰሜን ዕዝን ላይ በ45 ደቂቃ ውስጥ መብረቃዊ ጥቃት በመፈጸም ከጥቅም ውጭ አድርገናዋል” ሲሉ የተናገሩት አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸውን ጨምሮ አራት ከፍተኛ የሕወሃት አመራሮች ከነአጃቢዎቻቸውና ጠባቂዎቻቸው ሲደመሰሱ ዘጠኝ ደግሞ በቁጥጥር ስር ዋሉ ሲሉ የመከላከያ ሰራዊት ሃይል ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብርጋዴል ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት መግለጫ አስታወቁ።

የጀኔራል ተስፋዬ አያሌውን ቃል ጠቅሶ ኢዜአ ማምሻውን በሰበር ዜና እንደዘገበው ከአቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ሥራ አስኪያጅና የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዘርአይ አስገዶምን ጨምሮ በርካቶች ተደምስሰዋል ብሏል።

በተጨማሪም የድምጸ ወያኔ ሃላፊ የነበሩት አቶ አበበ ገብረመድህን እንዲሁም አቶ ዳንኤል አሰፋ የተባሉ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ የነበረ ከሹፌሮቻቸውና ከጥበቃዎቻቸው ጋር በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌደራል የጸጥታ ተቋማትና በትግራይ ሕዝብና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በተደረገ የተቀናጀ ዘመቻ መደምሰሳቸውን ብርጋዴል ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ለኢዜአ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የትግራይ ክልል አፈ ጉባኤ የነበሩት ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ እና የቀድሞ የትግራይ ክልል ከተማ ልማት ቢሮ ሃላፊና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ የነበሩ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ፣

የማረት ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ፣ የክልሉ ንግድ ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ገብረመድህን ተወልደ፣ የክልሉ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ወልደጊዮርጊስ ደስታ፣በሱዳን የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር አባዲ ዘሙ የመለስ አመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንትና የኢፈርት ቦርድ ሃላፊ የነበሩት አቶ ቴዎድሮስ ሃጎስ፣ የክልሉ ምክር ቤት ህግ አማካሪ የነበሩት ወይዘሮ ምህረት ተክላይ እና

የክልሉ የንብረትና ግዢ ሥራ ሂደት ሃላፊ የነበሩት አቶ ብርሃነ አደም መሃመድ ሁሉም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጄብርጋዴል ጀኔራሉ ገልጸዋል።

XS
SM
MD
LG