በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተፈናቃዮች ቁጥር ማሻቀብ በጤናው ዘርፍ ላይ የፈጠረው ተጽእኖ


የተፈናቃዮች ቁጥር ማሻቀብ በጤናው ዘርፍ ላይ የፈጠረው ተጽእኖ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:20 0:00

የተፈናቃዮች ቁጥር ማሻቀብ በጤናው ዘርፍ ላይ የፈጠረው ተጽእኖ

ደብረ ብርሃን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ እያስተናገደች ከመኾኗ ጋራ ተያይዞ፣ የከተማዋ የጤና ተቋማት መደበኛ የሕክምና አገልግሎት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን፣ የአስተዳደሩ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ሕክምና ለመስጠት ጥረት ቢደረግም፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነት በመኖሩ፣ ተፈናቃዮች የሕክምና አገልግሎት እያገኙ ያሉት፣ ከመጠለያ ጣቢያዎች ውጪ በሚገኙ የጤና ተቋማት እንደኾነ፣ የጤና መምሪያው ገልጿል፡፡

20ሺሕ የሚገመቱ ተፈናቃዮች ተጠልለውበታል ለሚባለው ቻይና ካምፕ ቅርብ የኾነው የጠባሴ ጤና ጣቢያ፣ ማስተናገድ ከሚገባው በላይ ቁጥር ያላቸውን ሕሙማን እያስተናገደ መኾኑም ተመልክቷል፡፡

በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ሕክምና እየሰጡ ያሉ አካላት፣ በተለይ በሕፃናት እና በእናቶች ላይ በምግብ እጥረት ሳቢያ የሚከሠቱ የጤና ችግሮች፣ ከሌሎች በሽታዎች ይልቅ አብላጫውን ቁጥር እንደሚይዙ ይናገራሉ፡፡

20ሺሕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች ተጠልለው እንዳሉበት በሚነገረው ቻይና ካምፕ አካባቢ የሚገኘው ጠባሲት ጤና ጣቢያ፣ የአካባቢውን ነዋሪ ጨምሮ ለበርካታ ተፈናቃዮች የሕክምና ግልጋሎት ይሰጣል፡፡

በዓመት 25 ሺሕ ሕሙማንን ለማስተናገድ የተቋቋመው የጤና ተቋም፣ ከ45ሺሕ በላይ ለመቀበል መገደዱን ያመለከቱት የጤና ጣቢያው ሓላፊ አስበ ደነቀ፣ የቁጥሩ ከፍተኛ መኾን፣ በአገልግሎት አሰጣጣችን ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል፤ ብለዋል፡፡

በጤና ጣቢያው፣ ለሕክምና የሔዱና ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡ የመንግሥት ሠራተኛ፣ ወደ ሐኪሙ ለመቅረብ ለአራት ሰዓታት ወረፋ መጠበቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ጤና ጣቢያው፣ ከደረጃው በላይ በርካታ ሕሙማንን ማስተናገዱ፣ በተገልጋዩ ላይ ብቻ ሳይኾን፣ የጤና አገልግሎቱን በሚሰጡት ባለሞያዎች ላይም አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው ሓላፊው አምነዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ ጤና መምሪያ ሓላፊ በቀለ ገብሬ፣ ከተማዪቱ በርካታ ተፈናቃዮችን ማስተናገዷን ተከትሎ፣ በጤና ተቋማት እና በአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ የፈጠረው ጫና፣ የመንግሥት እና የረጂ ተቋማት ትኩረት እንደሚያሻው አመልክተዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ባሉበት መጠለያ ጣቢያ፣ በአጋር አካላት ድጋፍ፣ የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ቢኾንም፣ ከተፈናቃዩ ቁጥር መብዛት እና አጋር አካላቱ ከተሠማሩበት ውስን ዘርፍ አንጻር፣ አገልግሎቱን ማስፋት እንዳልተቻለ አብራርተዋል፡፡

በቻይና ካምፕ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ፣ ሕክምና እና ምርመራ ይሰጥባቸዋል፤ ተብለው ወደተዘረጉት ድንኳኖች በደረስንበት ወቅት፣ ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት፣ ለሚያጠቡ እና ለነፍሰ ጡር እናቶች፣ የምግብ እጥረት ልኬታ በመደረግ ላይ ነበር፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ሓላፊ አቶ በቀለ፣ የአብዛኞቹ ተፈናቃዮች የጤና ችግር፣ ከግል እና ከአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ጋራ የተያያዘ እንደኾነ ይናገራሉ፡፡

በቻይና መጠለያ ጣቢያ እየሠሩ ያሉት የጤና ባለሞያ በለጠ ዓለማየሁ ደግሞ፣ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ አብላጫው የጤና ችግር፣ ከምግብ እጥረት የተነሣ እንደኾነ ነው የሚያስረዱት፡፡

በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የሚሰጠውን የምርመራ አገልግሎት ለማግኘት ከተሰበሰቡት አንዷ፣ ከወለጋ መኮፋ አካባቢ ተፈናቅለው መምጣታቸውን የሚገልጹት ካሳነሽ አሰን ናቸው፡፡ ሁለት ዓመት ያልሞላት ልጃቸውን እንደያዙ ነበር ያገኘናቸው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮ(OCHA)፣ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ወቅታዊ ሪፖርቱ፣ በአጋር አካላት እና በምግብ አቅርቦት እጥረት ምክንያት፣ በዐማራ ክልል መካከለኛ እና አጣዳፊ የምግብ እጥረት፣ እንዲሁም ከፍተኛ እና አጣዳፊ የምግብ እጥረት ላለባቸው ሕፃናት ምላሽ ለመስጠት ፈታኝ መኾኑን ገልጿል፡፡ ይህም በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን እንደሚካያትት አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG