በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በተፈናቃዮች በተጨናነቁት የደብረ ብርሃን መጠለያ ካምፖች የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከሠተ


በተፈናቃዮች በተጨናነቁት የደብረ ብርሃን መጠለያ ካምፖች የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከሠተ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:18 0:00

በተፈናቃዮች በተጨናነቁት የደብረ ብርሃን መጠለያ ካምፖች የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከሠተ

በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኙ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፖች ውስጥ የኩፍኝ ወረርሽኝ እንደተከሠተ፣ የከተማ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የኩፍኙ ወረርሽኝ ከተከሠተ፣ ሁለት ሣምንት መቆጠሩን የገለፁት የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ሓላፊ አቶ በቀለ ገብሬ፣ እስከ አሁን 80 ሰዎች በኩፍኝ መያዛቸውን ገልፀዋል።

በበሽታው የተያዙት ሰዎች ቁጥር፣ የመምሪያ ሓላፊው ከተናገሩት እንደሚበልጥ፣ በልዩ ልዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ይናገራሉ፡፡

በበሽታው እስከ አሁን የሞት አደጋ አለመድረሱንና እንዳይስፋፋ ግን፣ 10ሺሕ ለሚደርሱ ተፈናቃዮች ክትባት ሲሰጥ እንደቆየ፣ ሓላፊው አክለው ገልጸዋል፡፡

20ሺሕ ተፈናቃዮች ይኖሩበታል በሚባለው ቻይና ካምፕ፣ የተፈናቃዮቹ አስተባባሪ የሆኑት ቤትዬ ደርቤ፣ የኩፍኙ ክሥተት አሳሳቢ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉና በጤናው ዘርፍ እንደሚሠሩ የተናገሩ አንድ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው፣ “በሽታው ከመጠለያ ጣቢያዎቹ ውጭ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት አድሮብናል፤” ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የመጠለያ ካምፖች አቅንቶ በነበረበት ወቅት ያናገራቸው ተፈናቃዮች፥ በቂ የመጸዳጃ፣ የውኃ፣ የምግብ እና የመጠለያ አቅርቦት በሌለበት በማንኛውም ሰዓት ወረርሽኝ ሊከሠት ይችላል፤ የሚል ስጋት እንዳለባቸው፣ ተፈናቃዮቹ መናገራቸውን ዘግቦ ነበር፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ልየ ዞኖች ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኙ ስድስት መጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩ ተፈናቃዮች ቁጥር 30ሺሕ እንደሚደርስ፣ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG