በደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ አንድ የማዕድን ማውጪያ ጉድጓድ ውስጥ 60 አስከሬኖችን ማውጣቱን የሀገሪቱ ፖሊስ ዛሬ አስታውቋል። ሕገ ወጥ ያላቸውን ማዕድን ቆፋሪዎች 2.6 ኪ ሜ ከሚረዝመው ጉድጓድ ለማውጣት ፖሊስ ለወራት ሲጥር ቆይቷል። አንድ መቶ ስድስት ሰዎችን ማዳኑንም ፖሊስ አስታውቋል።
ከጆሃንስበርግ 140 ኪ.ሜ. ደቡብ ምዕራብ ርቀት ላይ ከሚገኘው የማዕድን ማውጪያ ሥፍራ ጉድጓድ ውስጥ ከመቶ በላይ ሰዎች ሞተው ሊሆኑ እንደሚችሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በማዕድን ቁፋሮው በአብዛኛው የሚሳተፉት ከጎረቤት ሃገራት የሚመጡ ስደተኞች ሲሆኑ፣ ነዋሪዎች ወንጀል በመፈጸም ይከሷቸዋል።
በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በጉድጓዱ ውስጥ ሊገኙ እንደሚችሉ ፖሊስ ቢገልጽም፣ በእርግጠኝነት ቁጥራቸውን ለማወቅ ግን አስቸጋሪ እንደሚሆን አመልክቷል።
ለማዕድን ቆፋሪዎቹ ከሚሟገት ቡድን ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል የደረሰው ቪዲዮ አስከሬኖች ሊሆኑ እንደሚችሉ የተገመቱና በደረዘን የሚቆጠሩ በጨርቅ ተጠቅልለው አሳይቷል።
ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ ፖሊስ ባደረገው ዘመቻ ሕገ ወጥ ናቸው ያላቸውን 1ሺሕ 500 የሚሆኑ ማዕድን ቆፋሪዎች መያዙን አስታውቋል። 121 የሚሆኑት ወደመጡበት ሃገራት እንዲመለሱ መደረጉንም ፖሊስ አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም