ዳዊት ከመንግሥት ጫና ቢደረግበትም በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃና ሚዛናዊ ዘገባ ህዝብን በማስነበብ አስተዋጽዖው ባለፈው ዓመት በእንግሊዝኛ ስሙ ምሕፃሩ ሲፒጄ ተብሎ የሚታወቀሉ የጋዜጠኞች ደህንነት ተሟጋቹ ቡድን ተሸላሚ እንደነበር ይታወቃል።
ዳዊት ከበደ ከአወዛጋቢው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት በኢትዮጵያ መንግሥት ታስረው በይቅርታ ከተፈቱት አንድ መቶ የሚገመቱ ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኞች አንዱ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን “ያ ይቅርታ ተነስቶ እንደገና የመታሰር አዝማሚያ ስለተጋረጠብኝ ለመሰደድ ወሰንኩ” ብሏል።
ጋዜጠኛ ዳዊት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኘው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በርዕሰ አንቀፁ እንዲሁም የመንግሥት ደጋፊ የሆነው ዛሚ ራዲዮ ጋዜጠኛው ”ከአሸባሪ ቡድኖች” ጋር ግንኙነት አለው የሚል ዘገባ በማሠራጨት መንግሥት ይቅርታውን እንዲያነሳ ቅስቀሣ እንዳደረጉና የይቅርታ ኮሚሽኑም ለዚሁ እየተዘጋጀ እንደነበር ከፍትህ ሚኒስቴር የታመኑ ምንጮች መስማቱን ዳዊት ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ገልጿል።
የፌዴራል አቀቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ ዛሬ ለብሉምበርግ ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ “ዳዊት ላይ እርምጃ የመውሰድ ዕቅድ አልነበረም” ብለዋል።
የፍትህ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ደሣለኝ ተረሣ “ዳዊት የተሳሳተ መረጃ ደርሶት ሊሆን ይችላል” ያሉትን ጠቅሶ ብሉምበርግ ዘግቧል።
ለተጨማሪ ትዝታ በላቸው ከጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ ያዳምጡ።