በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዓመታዊው የወግ አጥባቂዎች ጉባኤ ላይ ጄዲ ቫንስ ለአውሮፓ ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ


በዓመታዊው የወግ አጥባቂዎች ጉባኤ ላይ ጄዲ ቫንስ ለአውሮፓ ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:59 0:00

በዓመታዊው የወግ አጥባቂዎች ጉባኤ ላይ ጄዲ ቫንስ ለአውሮፓ ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ

በዓመታዊው የወግ አጥባቂ አቀንቃኞች የፖለቲካ ጉባኤ ወይም በምጻሩ ’ሲፓክ’ ላይ ትላንት ሐሙስ ንግግር ያደረጉት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝደንት ጄዲ ቫንስ፣ የውጪ ጉዳዮችን በተመለከተ ያላቸውን ሐሳብ ይፋ አድርገዋል። ምክትል ፕሬዝደንቱ ንግግር ባደረጉበት የወግ አጥባቂዎቹ ጉባኤ ላይ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕን አጀንዳ የሚደግፉ የውጭ ሃገራት ፖለቲከኞችም ተገኝተዋል።

በዚህ ጉባኤ ላይ አሜሪካ በምክትል ፕሬዝደንቷ ጄዲ ቫንስ በኩል ለአውሮፓ ማስጠንቀቂያዋን ልካለች፡፡

“ከአውሮፓ ጋራ አስፈላጊ የሆነውን አጋርነት እንቀጥላለን። ነገር ግን የአጋርነታችን ጥንካሬ ማኅረሰባችንን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ በመምራት ላይ ይወሰናል” ብለዋል ጄዲ ቫንስ።

በዚህ ዓመቱ ጉባኤ ላይ ከሌሎች ሃገራት የመጡ ቀኝ ዘመም መሪዎችም ተገኝተዋል። ከአርጀንቲና፣ እንግሊዝ፣ ፖላንድ፣ ሃንጋሪ፣ እና ጣሊያን የፖለቲካ መሪዎች ተገኝተዋል።

ተንታኞች በበኩላቸው ጉባኤው አሜሪካ ከረዥም ጊዜ አጋሮቿ መነጠሏን በግልጽ ያመለከተ ነው ባይ ናቸው።

ጂም ከስለር ‘ሰርድ ዌይ’ የተሰኘው ተቋም ምክትል ፕሬዝደንት ናቸው። ስለጉባኤው ሲናገሩም፣ “በሲፓክ ጉባኤ ላይ እየሆነ ያለውን ከምር መመልከት አለብን። በዚህ ጉባኤ ላይ እየታዘብን ያለው አሜሪካ ከተለምዶ አጋሮቿ፤ አውሮፓ፣ ኔቶ፣ እየተነጠለች መሆኑን ነው። ይህ ለ80 ዓመታት የቆየ አጋርነት እየተሰነጣጠቀ ይገኛል። እናም ይህ ለአሜሪካውያንም ሆነ ለአውሮፓ አሳሳቢ ነው” ብለዋል።

የትረምፕን ሃሳብ የሚቃወሙት ሁሉም አውሮፓውያን አይደሉም። ባላዝስ ኦርባን የሃጋሪው ጠቅላይ ምኒስትር ቪክቶር ኦርባን የፖለቲካ ሃላፊ ሲሆኑ በጉባኤው ላይ ሲናገሩም፣ “ጦርነቱ ይቁም። ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ልክ ናቸው። ጠቅላይ ምኒስትራችንም እንዳሉት፣ ይህ ጦርነት መቆም አለበት፣ ምክንያቱም የትም አያደርሰንም። እብደት ነው። በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች አልቀዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ዳያና ኢቫኖቪቺ ሶሶዋካ የአውሮፓ ፓርላማ ዓባል ናቸው። በሮሜንያ የቀኝ አክራሪ ፓርቲን ይመራሉ። በትረምፕ አስተዳደር በጉባኤው እንዲሳተፉ እንደተጋብዙ ለቪኦኤ አስታውቀዋል። ይህም ለእርሳቸው የመጀመሪያው ሲፓክ ጉባኤ ነው። ከትረምፕ ጋራ የሚጋሩትን አቋም በተመለከተ ተናግረዋል። በዚህ አቋማቸውም የሮሜንያ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤት በሃገሪቱ ከተደረገው የ2024 ፕሬዝደንታዊ ምርጫ አግዷቸዋል።

“ምክንያቱም የአውሮፓ ኅብረትን የሚቃወሞ ሃሳቦች አሉኝ። ጦርነትን የሚፈጥረው ኔቶን የሚቃወሙ ሃሳቦች አሉኝ። በነጻነት ሃሳቤን ስለምገልጽ፣ በኮቪድ ክትባት ላይና የፊት ጭንብል(ማስክ) በመጠቀም ላይ ተቃውሞ ስላለኝ ነው። እናነተ የአሜሪካ ድምጽ እንደሆናችሁ ሁሉ እኔም የሮማኒያ ድምፅ ነኝ። ሕግ መንግሥታዊ ያልሆነ ሃሳብ ስላለኝ፣ መምረጥ አትችይም ተባልኩ” ይላሉ ሶሶዋካ።

የሲፓክ ጉባኤ ትረምፕ በወግ አጥባቂው ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛውን ሥፍራ እንዲቆናጠጡ አስችሏል። በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በተካሄደው ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል። በዚኽኛውም ጉባኤ ላይ ቅዳሜ ንግግር እንደሚያደርጉ ፕሮግራም ተይዟል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG