በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ ከ5 በታች ለሆኑ ህጻናት የኮቪድ-19 ክትባት በማዘጋጀት ላይ ነች


ፎቶ ፋይል፦ የዋይት ኃውስ የኮሮናቫይረስ ምላሽ አስተባባሪ አሺሽ ጃህ
ፎቶ ፋይል፦ የዋይት ኃውስ የኮሮናቫይረስ ምላሽ አስተባባሪ አሺሽ ጃህ

እየተገመገሙ ያሉት ሁለት ክትባቶች በሁለቱም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ፈቃድ ካገኙ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ አሜሪካውያን ህጻናት እአአ ከሰኔ 21 ቀን ጀምረው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት መከተብ እንደሚችሉ የዋይት ኃውስ ከፍተኛው የኮቪድ-19 ጉዳይ ባለሥልጣን አስታወቁ፡፡

የዋይት ኃውስ የኮሮናቫይረስ ምላሽ አስተባባሪ አሺሽ ጃህ በሰጡት ቃል “ብዙ ወላጆች ህጻናት ልጆቻቸውን ለማስከተብ እንደሚጓጉ እናውቃለን፡፡ እየተከናወነ ያለው ሂደት ዓላማም በትክክል እንዲከናወን ማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ ነው” ብለዋል፡፡

ከዛሬ አርብ ጀምሮ ፌዴራል መንግሥቱ ክትባቱን ለሚያዝዙ ክፍለ ግዛቶች መድሃኒት ቤቶች የማኅበረሰብ የጤና ማዕከሎች እና የፌዴራል መንግሥት ተቋማት አስር ሺህ ምጥን ክትባቶች አንደሚያዘጋጅ ዶክተር ጃህ ገልጠዋል፡፡

“የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር ፈቃድ ሲሰጥ ክትባቶቹን መላክ ይቻላል የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማእከል ሲፈቅድ ደግሞ ህጻናቱን መክተብ መጀመር ይቻላል፡፡” ብለዋል፡፡ ሂደቱ በተሳለጠ መንገድ ከተከናወነ እአአ ከሰኔ (ጁን) 21 ጀምሮ ህጻናቱ ሊከተቡ ይችላሉ ብለዋል የዋይት ሀውስ የኮሮናቫይረስ ምላሽ አስተባባሪው ዶክተር አሺሽ ጃህ፡፡

ባሁኑ ወቅት በሁለት ጊዜ የሚሰጡትን ክትባቶች እና በማስከተልም ማጠናከሪያውን ክትባት መከተብ የሚችሉት ከአምስት ዓመት በላይ የሆኑ ልጆች ብቻ ናቸው፡፡ ክትባቱ ለህጻናቱ እንዲሰጥ ከተፈቀደ ለአዋቂ በሚሰጠው መጠን ሳይሆን በትንሹ ተመጥኖ አንደሚዘጋጅ ዶክተር ጃህ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ወር ቶኪዮ ውስጥ በተካሄደው በምህጻር “ኳድ” ተብሎ የሚጠራው የአራት ሀገሮች የአራትዮሽ የፀጥታ ጉዳይ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ከባድ ችግር ላለባቸው ሀገሮች የኮቪድ-19 ማጠናከሪያ ክትባቶች እና ለህጻናት የሚሆኑ ክትባቶች አንደምትልክ ቃል ገብታለች፡፡

XS
SM
MD
LG