የአክስዮን ገበያውን የኮሮናቫይረስ ፍርሃት ተዛመተበት። በርካታ ክፍለ ግዛቶች የንግድ ድርጅቶችን በትዕዛዝ መዘጋት በጀመሩባት በዩናይትድ ስቴትስ የኑሮ እንቅስቃሴዎች ቀጥ ሲሉ ጊዜ አልፈጀባቸውም። የዎል ስትሪት የኒውዮርክ የአክስዮን ገበያም ዛሬ ጠዋት አሽቆልቁሏል።
የሃገሪቱ የማዕከላዊ ባንክ ፌዴራል ሪዘርቭ በአንድ ቀን ቀደም ብሎ ከወትሮው ለየት ያለ ዕርምጃ ቢወስድም የአምስት መቶ ትላልቅ ኩባኒያዎችን አክስዮን ክንዋኔ የሚከታተለው ኤስ ኤንድ ፒ 500 ገበያው በተከፈተ በሰኮንዶች ውስጥ የስምንት ከመቶ የዋጋ ውድቀት አሳይቶ የንግድ እንቅስቃሴው ወዲያውኑ ለአስራ አምስት ደቂቃ ተቋርጧል።
ገበያው እንደገና ሲቀጥል እንደገና የዋጋ ውድቀት አሳይቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓለምቀፉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ የኩባኒያዎች ገቢን ይመታል የሚለው ስጋት በገነነበት በዚህ ወቅት ፊዴራል ሪዘርቭ ( ማዕከላዊ ባንኩ ) ትናንት አጣዳፊ ዕርምጃ ወስዶ የወለድ መጠኑን ወደዜሮ ገደማ ዝቅ አድርጎታል።
ያም ሆኖ ግን የእስያ ገበያዎች ዛሬ በከፍተኛ መጠን የዋጋ ማሽቆልቆል ማሳየታቸው ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በኒውዮርክ ዎል ስትሪ የተፈጠረውን አመላክቷል።
ትናንት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ከጂ ሰባት አባል ሃገሮች መሪዎች ጋር ጸረ ኮሮና ጥረቶችን ለማስተባበር ስለሚቻልበት መንገድ በቪዲዮ አማካይነት በተካሄደ ውይይት ተሳትፈዋል። ከዚያም በማስከተል ሃምሳዎቹም የዩናይትድ ስቴትስ ክፍለ ግዛቶች አገረ ገዢዎች ጋር በዚሁ ጉዳይ በቪዲዮ አማካይነት ስብሰባ አድርገው ተነጋግረዋል።
ዛሬ ዋይት ሃውስ በጠዋት የፀረ ኮሮና ቫይረስ ግብረ ኃይሉ ገለፃ ያደርጋል ብሎ የነበረ ሲሆን በኋላ ግን ወደከሰዓት በኋላ አዙሮታል።
ፕሬዚደንቱና የአስተዳደራቸው አባላት በህዝቡ ዘንድ ያለውን ፍራቻ ለማብረድ እየሞከሩ ናቸው። ሰው በፍርሃት ምግብና ሌላም አስቤዛ በብዛት እየገዛ እያጠራቀመ በመሆኑ መደብሮች ባዶቸውን የቀሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ