ዋሺንግተን ዲሲ —
በዩናይትድ ስቴትስ የኮቪድ-19 ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለበት የካሊፎርኒያ ግዛት በሚገኙ ሁለት አካባቢዎች ከማክሰኞ የሚጀምር ከቤት ያለመውጣት ክልከላ ይታወጃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
የግዛቷ አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሰም በትላንትናው ዕለት እንደተናገሩት ሳን ጃጁዊን ቫሊ እና ደቡብ ካሊፎርኒያ አካባቢ የፅኑ ህሙማን ማቆያ ቦታዎች እና ሆስፒታሎች በሞሉበት ሁኔታ ከሦስት ሳምንት በፊት ተጥለው የነበሩት ክልከላዎች እንደሚራዘሙ ግልፅ ነው ብለዋል።
ሁኔታው በጣም እየከፋ ከመሄዱ የተነሳም ሆስፒታሎች አስቸኳይ ርዳታ የሚሹ በሽተኞችን እየመለሱ ሲሆን በከፍተኛ ሁኔታ እየመጡ ያሉትን የኮቪድ 19 በሽተኞችን ለማስተናገድ ድንኳኖች ተክለዋል።
የካሊፎርኒያ ክፍለ ግዛት በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ የወረርሽኙ ማዕከል ሆናለች። ከጆንስ ሆፕኪንስ የኮሮና ቫይረስ መረጃ ማዕከል የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየውም እሳሁን 2 ሚሊዮን 192 ሺህ 694 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሲኖሩ 24 ሺሕ 419 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።