የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኮሮናቫይረስ እንደያዛቸው ገለጡ። ኦባማ በትዊተር ትናንት ባወጡት ቃል" ጉሮሮዬን ለሁለት ቀን ያህል ከመከርከር ስሜት በስተቀር ደህና ነኝ" ብለዋል። ባለቤታቸው ሚሼል ኦባማ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ኦባማ አክለው ገልጸዋል።
"እኔና ሚሼል ሙሉውን ክትባት መከተባችን እና ማጠናከሪያውን መውሰዳችን በጅቶናል" ያሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በዩናይትድ ስቴትስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም አሜሪካውያን መከላከያ ክትባቱን መከተብ እና ማጠናከሪያውንም መውሰዱ በጽኑ ላለመታመም እና ቫይረሱንም ወደሌላ ሰው ላለማስተላለፍ የሚረዳ መሆኑን ያስታውሰናል" በማለት ምክር ለግሰዋል።
በሌላ የኮቪድ-19 ዜናዎች የቻይናዋ ሲሊከን ቫሊ ተብላ የምትታወቀዋ ሼንዜን ከተማ የኮሮናቫይረስ ተጋላጮች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ መዘጋቷ ተገለጠ። ከተማዋ ፎክስኮንን ጨመሮ በርካታ የዩናይትድ ስቴትሱ አፕል ኩባኒያ አቅራቢዎች ማምረቻዎች ይገኙባታል።
ባሳለፍነው ሳምንት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለኮሮናቫይረስ የተጋለጠው ሰው ቁጥር ወደሰላሳ አምስት ሺህ ባለፈው ጥር አጋማሽ በአማካይ 800 ሺህ ገደማ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ሲዲሲ ባወጣው ሪፖርት መሰረት ከጠቅላላው አዋቂዎች ሰባ አምስት ነጥብ ሁለት ከመቶው ሙሉውን ክትባት ወስደዋል። ከዚያ ውስጥም አርባ ሰባት ነጥብ ሰባት ከመቶው ማጠናከሪያ ክትባቱንም ተከትበዋል።