በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኮሮናቫይረስ መንሠራፋቱን ቀጥሏል፤ ወባ እያሰጋ ነው


የብሄራዊው የተላላፊ ደዌዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አንተኒ ፋውቺ
የብሄራዊው የተላላፊ ደዌዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አንተኒ ፋውቺ

በዩናይትድ ስቴትስ ለኮሮናቫይረስ የሚጋለጠው ሰው ቁጥር በመጭዎቹ ሣምንታት ውስጥ “በከፍተኛ መጠን ያሻቅባል” ብለው እንደሚጠብቁ የብሄራዊው የተላላፊ ደዌዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አንተኒ ፋውቺ አስታውቀዋል።

ባለፈው ሣምንት በተከበረው የምሥጋና ቀን በዓል ምክንያት የሰዉ ጉዞና መገናኘት በዝቶ በመታየቱ የተያዡ ቁጥር እየተደራረበ እንደሚጨምር ከኤቢሲ ቴሌቪዥን “ዝስ ዊክ” ፕሮግራም ጋር ቃለምልልስ ባደረጉበት ወቅት አሳስበዋል።

በሌላ ቃለምልልስ “ፌስ ዘ ኔሽን” ከሚባል የሲቢሲ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር የተነጋገሩት የዋይት ሃውስ የኮሮናቫይረስ ምላሽ አስተባባሪ ዴብራ ብሪክስ በዚህ የበዓል ወቅት ጉዞ ላይ የነበሩ ሁሉ “ለቫይረሱ ተጋልጠናል” ብለው እንዲያስቡና ዕድሜአቸው ከ65 ዓመት በላይ ከሆነና ሌሎች ነባር ህመሞች ካሏቸው ሰዎች ጋር ከመገናኘት እንዲቆጠቡ መክረዋል፤ በዚህ ሣምንት ውስጥ ምርመራ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ማሳሰቢያዎቻቸውን ያወጡት የዩናይትድ ስቴትስ ለኮሮናቫይረስ መጋለጥ ቁጥር ባለፈው ወር ኦክቶበር ውስጥ ከነበረው 1.9 ሚሊየን በእጥፍ አሻቅቦ በዚህ በተጠናቀቀው ኖቬምበር ከአራት ሚሊየን በላይ ቁጥር ያለው ሰው መያዙ ከተነገረ በኋላ ነው።

በዓለም ውስጥ ካለው ወደ 63 ሚሊየን የሚጠጋ ተጋላጭ 13.3 ሚሊየኑ የተመዘገበው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መሆኑን የጃንስ ሃፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የኮሮናቫይረስ መረጃ ማዕከል አመልክቷል።

ብራዚል በ9.4 ሚሊየን፣ ህንድ ደግሞ በ6.3 ሚሊየን ተጋላጭ ዩናይትድ ስቴትስን ተከትለው ሁለተኛና ሦስተኛ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኮቪድ 19 ምክንያት ብዙ የጤና አገልግሎቶች በመረባበሻቸው በዚህ ዓመት በወባ ሊደርስ የሚችለው የሞት ጉዳት ከኮቪድ ሊበልጥ እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት ሥጋቱን ገልጿል።

XS
SM
MD
LG