በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን ሦስተኛ ዙር የማጠናከሪያ ክትባት ሊሰጥ መሆኑን ይፋ አደረጉ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

ሙሉ በሙሉ ክትባት ለወሰዱ አሜሪካዊያን ሦስተኛ ዙር የማጠናከርሪያ ክትባት ሊሰጥ መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር አስታወቀ።

ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአሜሪካ ሕዝብ የፀረ ኮቪድ 19 ክትባት በተከተበበት በአሁኑ ሰዓት፤ ሁለተኛውን ክትባት ከተከተቡ ስምንት ወር ለሞላቸው አሜሪካውያን የማጠናከሪያ ሊሰጥ መሆኑን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ “ሁለተኛውን ክትባታችሁን ከወሰዳችሁበት ጊዜ በኋላ ስምንት ወር ሲሞላችሁ ማጠናከሪያውን ክትባት ውሰዱ፤ ክትባቱ በነጻ ነው የሚሰጠው፥ በሀገሪቱ ዙሪያ ካሉት ሰማንያ ሺህ የክትባት መስጫ ቦታዎች በአቅራቢያችሁ ካለው አንዱን መርጣችሁ መከተብ ትችላላችሁ። ቀላል ይሆናል” ብለዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ከፍተኛ ሳይንቲስቶች ክትባቱ አዲሱን የዴልታ ቫይረስ ዝርያ የመቋቋም ኃይሉ ከፍተኛ እንደሆነ ተረጋግጧል ብለዋል። ሆኖም ዓለም አንዱን ክትባት ለማግኘት ትግል በያዘበት በዚህ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ሦስተኛ የማጠናከሪያ ክትባት ለመስጠት መወሰኗ ከጤና ተቋማት ትችት አስከትሎባታል።

ዘ ዋን ካምፔይን የተባለው ድርጅት ባወጣው መግለጫ፤ “ገቢያቸው ዝቅተኛ በሆኑ ሃገሮች ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎች እና የጤና ሠራተኞች ሳይከተቡ ለጤነኞቹ እና አስቀድመው ለተከተቡት ሰዎች ተጨማሪ ክትባት መስጠት እጅግ የሚያስቆጣ ድርጊት ነው።” ሲል ነቅፏቸዋል።

“ባለጸጎቹ ሃገሮች ቫይረሱን ከዓለም ላይ የሚያስወግድ ዕቅድ ማውጣት እንዳልቻሉ የሚያሳይ ነው” ሲልም የበጎ አድራጎት ድርጅቱ አሳስቧል።

ጆኒ ኦትኖፍ የተባሉ ዘ ዋን ካምፔይን የተሰኘ ድርጅት አንቂ፤ “ይህ ለባለፀጋ ሃገሮች የሚቀርብ የሕሊና ጉዳይ ብቻ አይደለም። ይህ ሁኔታ በእርግጠኝነት ወረርሽኙ እንዲራዘም ያደርገዋል።” ብለዋል።

“የአንዳንድ ሃገራት መሪዎች፤ ብዙ ሃገራት የመጀመሪያ ዙር ክትባት እንኳን ሳያገኙ ዩናይትድ ስቴትስ ሦስተኛውን ክትባት ልታገኝ አይገባም እያሉ እንደሆነ አውቃለሁ።እኔ በዚህ አልስማማም።” ያሉት ፕሬዝዳንት ባይደን ዩናይትድ ስቴትስ ለሌሎች ሃገራት ከለገሰችውን የፀረ ኮቪድ 19 ክትባት አንፃር ትችቱ ምንም ቦታ እንደማይኖረው በመግለፅ ምላሽ ሰጥተዋል።

አያይዘውም “አሜሪካውያንን እየተንከባከብን የሌላውን ሃገር ሕዝብም በእኩል መርዳት እንችላለን። በሰኔ እና በሐምሌ 50 ሚሊዮን አሜሪካውያንን ከትበናል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ደግሞ 100 ሚሊዮን ክትባቶችን ለሌሎች ሃገራት ለግሰናል።” ብለዋል።

ይህ ውሳኔ ከዋሽንግተን የወጣው የበዛው የዓለም ህዝብ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት እሲያገኝ ድረስ ሁለተኛው የማጠናከሪያ ክትባት እንዲዘገይ የሚጠይቀው የዓለም የጤና ድርጅት ጥሪ ከቀረበ በኋላ ነው።

በሌላ በኩል በአንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጠውን የጆንሰን ኤንድ ጆንሰኑን ክትባት የተከተቡ ሰዎችም ተጨማሪ ማጠናከሪያ ክትባት መውሰድ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል። በዚህ ላይ ውሳኔ ለመስጠት በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት በጆንሰን ኤንድ ጆንሰኑ ክትባት ዙሪያ የሚሰባሰቡ መረጃዎችን ተመርኩዘው ውሳኔ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

የሃገሪቱ የተላላፊ በሽታዎች ከፍተኛው ባለሞያ እና የፕሬዚደንቱ የጤና ጉዳዮች አማካሪ ዶክተር አንተኒ ፋውቺ ክትባቱ የሚያስገኘው የሰውነት የተፈጥሮ መከላከያ ከጊዜ ጋር እንደሚዳከም እና በተለይም የቫይረሱን ዴልታ ዝርያ ለመቋቋም ማጠናከሪያ ክትባት ሊያስፈልግ እንደሚችል ያሉን ወቅታዊ መረጃዎች ያመለክታሉ ብለዋል።

“ቅድሚያ ትኩረት የምንሰጠው ጉዳይ የቫይረሱ ባህሪ እና የወረርሽኑ ሁኔታ ያለማቋረጥ እየተለዋወጠ ባለበት በዚህ ወቅት አሜሪካውያንን በሚገባ ውጢታማና ለረጅም ጊዜ በሚቆይ ክትባት ከኮቪድ አስራ 19 መጠበቅ ነው" ሲሉም አንተኒ ፋውቺ አስረድተዋል።

XS
SM
MD
LG