በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን አሜሪካ ውስጥ በኮቪድ የሞቱትን ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ዘከሩ


በዋይት ሐውስ በኮቪድ 19 ለመሞቱት 500 ሺ ሰዎች የተደረገ መታሰቢያ
በዋይት ሐውስ በኮቪድ 19 ለመሞቱት 500 ሺ ሰዎች የተደረገ መታሰቢያ

በዩናትድ ስቴትስ ውስጥ በኮቪድ 19 ህይወታቸው ያጡ ሰዎች ቁጥር 500ሺ መድረሱን ምክንያት በማድረግ ፕሬዚዳንት ባይደን በተገኙበት ዋይት ሀውስ ውስጥ ትናንት ምሽት የመታሰቢያ ሥነ ሥርዐት ተደርጓል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን በወረርሽኙ የሚወዷቸውን ሰዎች ለተጠነቁ ሰዎችና ቤተሰቦች የማጽናኛ መልኧክት አስተላልፋዋል፡፡ አገሪቱ ከዚህ አስከፊ ወረርሽኝም ነጻ እንደምትወጣም ቃል ሰጥተዋል፡፡

አሜሪካ በኮቪድ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ልክ 500ሺ መድረሱን ዘክራለች፡፡ የሀዘን ድባባ ባጠላበት የሰኞው ምሽት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ በዋይት ሀውስ ህንጻ በስተደቡብ በሚገኘው መተላለፊያ ደረጃዎች ላይ በጥቁር ጨርቅ ሰንደቅ ታጀበው በተቀጣጠሉ 500 ሻማዎች ፊት ለፊት ቆመዋል፡፡

ከፕሬዚዳንቱ ጋር ቀዳማዊት ዕመቤት ጂል ባይደን ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ከማላ ኻሪስ እና ባለቤታቸው ዳግ ኤምሆፍ ተገኝተል፡፡

ከፕሬዚዳንቱ ጋርም በአንድነት በመቆም የባህር ኃይሉ የሙዚቃ ጓድ ባሰማው “አሜዚንግ ግሬስ” በተሰኘው የቤተከርስቲያን ዜማ ስለሟቾቹ የህሊና ጸሎት አድርሰዋል፡፡

የዝማሬው ሙዚቃ እንደተጠናቀቀ፣ ወደ ካቶሊክ ቤተከርስቲያን አዘውትረው መሄዳቸው የሚነገርላቸው ባይደን፣ የመስቀል ምልክት በማሳየት አማትበዋል፡፡

ከዚህ ሥነ ሥርዐት ጥቂት ቀደም ብሎ ፕሬዚዳንት ባይደን ህይታቸውን በኮቪድ ላጡና የሚወዷቸውንም የተጠነቁ ቤተሰቦችን ለማሰብ አሜሪካውያን አብረዋቸው የህሊና ጸሎት በማድረግ እንዲዘክሯቸው ተማጽነዋል፡፡ ለተጎጂዎቹ ቤተሰቦችም በቀጥታ ባሰሙት ንግግር

“ጨርሶ የማይታሰብ ይመስላል ግን ቃል እገባላችኋለሁ፡፡ ስለተጠነቃችሁት ሰው ያላችሁ ትውስታ ወደ ፊታቸው የሚያመጣው እምባ መሆኑ ቀርቶ ፈግግታ እሚሆንበት ቀን ይመጣል፡፡” ብለዋል፡፡

በአሰቃቂ ሁኔታ የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ በሚገኘው ወረርሽኝ መካከል፣ ተጎጂዎችን የሚያጽናና አንዳችም ነገር ያለማድረግ ጭካኔም መቅረት ያለበት ስለመሆኑ ባይደን ተናግረዋል፡፡

“ብዙ አጽናኝ የሆኑ እምነትና ባህሎች ያግዙናል፡፡ የምንወዳቸውን እንድንዘክር ይረዱናል፡፡ ይሁን እንጂ ግን እነሱንም ማጽናኛዎች እንኳ አላገኘናቸውም ነበር፡፡ እንደ አገር ይህን ይዘን እንደዚህ ሆነን መቀጠል አይገባንም፡፡” ብለዋል፡፡

በኮቪድ የሞቱንን 500ሺ ሰዎች ለመዘከር ፕሬዚዳንት ባይደን ትናንት ሰኞ የዩናይትድ ሴትትስ ሰንደቅ ዓለማ በሁሉም የፌደራል መንግሥት ህንጻዎች ላይ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አዘዋል፡፡በአገሪቱ መዲና በዋሽንግተን የሚገኘው ብሄራዊ ካቴድራልም ደወሉን 500 መቶ ጊዜ በመደወል በወረርሽኙ የተሰውትን አስቧል፡፡

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናል ትራምፕ “ወረርሽኙን በቁጥጥር ሥር አውለነዋል፡ ብለው የተናግሩት” ልክ የዛሬ ዓመት ነበር፡፡

ትራምፕ ኢንዲያና ወደ ተባለው ክፍለ ግዛት ለመሄድ ሲነሱ እዚያው ዋይት ሀውስ ጊቢ ውስጥ ከሚገኘው መስክ ላይ ሆነው ነበር “በጣም ይገርማችኋል ምንም የሞተ ሰው የለንም፡፡” ያሉት፡፡

በዩናይትድ ስቴት ለመጀመሪያ ጊዜ በቫይረሱ ህይወቱ ያለፈ ሰው መኖሩ የታወቀው ግን ትራምፕ ይህን ካሉበት ሁለት ሳምንታት በፊት መሆኑ ታውቋል፡፡

ባለሥልጣናቱም፣ በካሊፎርኒያ ሳንሆዜ ነዋሪ የነበሩት የ57 ዓመቷ ፓትሪሺያ ዳውድ በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፉ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገሩት እኤአ በመጋቢት ወር 2020 ላይ ነበር፡፡

ግማሽ ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የወረረሽኙ አስከፊ ጥላ ባጠላበትና የቫይረሱም ዝርያ ተለዋዋጭ እየሆነ መታየት በጀመረበት በዚህ ወቅት፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ባለሥልጣናት ተስፋ መኖሩን እየተናገሩ ነው፡፡

ባለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ፣ በአገሪቱ የታየው የሟቾች ቁጥር በአማካይ ቀንሶ መታየቱን በአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕከል ድሬክተር ዶ/ር ሮሼል ዎለንስኪ ተናግረዋል፡፡

በመላው አገሪቱ የሚደረገው የኮቪድ 19 ክትባት ዘመቻም በመካሄድ ላይ ሲሆን የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ወደ 13 ከመቶ የሚሆኑ ሰዎች መውሰዳቸውም ተገልጿል፡፡ ይህ መሆኑ በአንዳንድ ክፍለ ግዛቶችም የተከሰተው አደገኛው የክረምት አየር ጠባይ ባለበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕክል ድሬክተር ዶ/ር ሮሼል ዎለንስኪ በሰጡት መግለጫ፣ አሁንም በየቀኑ 66ሺ የሚሆኑ ሰዎች ለቫይረሱ የተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የፕሬዚዳንቱ ዋነኛው የህክምና ጉዳዮች አማካሪ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺም፣ “አሁንም ቢሆን ያለንበት ሁኔታ ተቀባይነት የሌለውና ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመሆኑ ጥንቃቄው ሊለየን አይገባም” ብለዋል፡፡

በመላው ዓለም በኮረና ቫይረስ ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል ዩናይትድ ስቴትስ ወደ 20 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ የምትወስድ ሲሆን፣ ከዓለም ህዝብ ቁጥር ሲስተያይ፣ ያላት የህዝብ ብዛት ድርሻ ግን 4 ከመቶ ብቻ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ይህ ቀውስ፣ በከፊል በፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ወጥነት የጎደለው የፌደራል መንግሥት ምላሽ በመኖሩ ምክንያት የተከሰተ መሆኑም ተነስቷል፡፡

ትራምፕ ከሥልጣናቸው እስከተሰናበቱበት ጥር 20 ድረስ ከጤና አማካሪዎቻቸውና ባለሙያዎች ጋር ያልተስማሙ ሲሆን የወረርሽኙንም ጉዳይ 50ዎቹ የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች በየግላቸው በተናጥል እንዲወጡት ትተውላቸው የሄዱ መሆኑን ተነግሯል፡፡

የፎሎሪዳ ግዛት አስቸኳይ ጉዳዮች አስተዳደር ድሬክተር ጃሬድ ሞስኮዊትዝ እንደሚሉት የባይደን አስተዳደር “ብዙ ውጥንቅጥ ጉዳዮችን” ተረክቧል፡፡

2020 ዓመተ ምህርት ከአሜሪካውያን አማካይ የነፍስ ወከፍ የህይወት ዘመን ላይ አንድ ዓመት የሚሆነውን ይዞት ሄዷል፡፡ ይህ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፐሎሲ፣ ምክር ቤቱ አጣዳፊውን የኮቪድ እርዳታ ላይ አስመልከቶ ውሳኔውን በአስቸኳይ እንዲያስተላለፍ ለመገፋፋት፣ በትናንትናው እለት ባወጡት መግለጫ የወረርሽኙን ሁኔታ “እጅግ ዘግናኝ የሆነ እልቂትና ሊረዱት እንኳ የማይቻል ሀዘንን” የፈጠረ ነው ብለውታል፡፡

አገሪቱ ወረርሽኙ ካሳደረባት ሁሉን አቀፍ ተጽእኖ እንድታገግምና በሽታውን ለመከላከል እንትድትችል ፕሬዚዳንት ባይደን የ1.9 ትሪሊዮን ዶላር እቅድ መንደፋቸው ይታወቃል፡፡

አንዳንዶቹ የምክር ቤት አባላት ግን ከገንዘቡ መጠን በተጨማሪ ምን ምን ነገሮች ሊሸፈኑ እንደታሰቡ ግልጽነት ይጎድለዋል በማለት ጥያቄዎቻቸውን እያቀረቡ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደንም በትናንቱ ንግግራቸው

“እኔ የአሜሪካ ህዝብን ለማዳን የበለጠ ረከስ ያለና የተሻለ ፕላን ያለበትን የትኛውንም ሀሳብ ለመስማት ዝግጁ ነኝ፡፡ ካሉ በኋላ አስክተለውም ይሁን እንጂ ግን የምናወጣው እቅድ ማንን እንደሚረዳና ማንን እንደሚጎዳ በግልጽ ለይተን መመልከት ይኖርብናል” ብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG